ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ትገኛለች – ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

AMN – ጥቅምት 27/2017

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ትገኛለች ሲሉ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት እንደነበርም ገልጸዋል።

በጉባዔው ለመሳተፍ ለመጡ ለአፍሪካ አገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና የተቋማት ኃላፊዎች የእራት ግብዣ ተደርጓል።

በመርሐ-ግብሩም ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የሴራሊዮን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ፣ የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴኤታ ሸኸ ሻክቦት ቢንናህያን ተገኝተዋል።

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በዚሁ ጊዜ፣ ረሃብ በርካታ የአፍሪካ አገራትን የፈተነ እና ችግር ፈቺ መፍትሔ የሚሻ የጋራ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያም ረሃብ የሚያስከትለውን ጉዳት በጽኑ ትገነዘባለችም ብለዋል።

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ በስንዴ ራሷን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ መላክ የሚያስችል አቅም መፍጠሯን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እያበረከቱ ያለውን የመሪነት ሚና አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደሮችን በቅርበት ከማገዝ ጀምሮ በግብርናው ዘርፍ ስትራቴጂካዊ ለውጦችን አስመዝግበዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑንም መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ተናግረዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review