ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረጉ የልማት እንቅስቃሴ ውጤቶችን በተግባር እያሳየች ነው – ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረጉ የልማት እንቅስቃሴ ውጤቶችን በተግባር እያሳየች ነው – ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ

AMN ግንቦት 15/2017

ኢትዮጵያ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረጉ እና የአጀንዳ 2063 የልማት ግቦችን የሚያሳኩ የልማት እንቅስቃሴ ውጤቶችን በተግባር እያሳየች መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

ከግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በአፍሪካ ሕብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሄድ የቆየው 20ኛው የዓለም ሥራ ድርጅት አህጉራዊ ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል፡፡

ከ50 በላይ የዓለም ሀገራት ተወካዮች፣ 30 የአፍሪካ ሚኒስትሮች፣ ከሁለት ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የታደሙበት ስብሰባ የአዲስ አበባ ቃል ኪዳን በሚል የጋራ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ጉባኤውን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ በአፍሪካ ማንኛውም የልማት ሥራ የሥራ ዕድል ፈጠራን ታሳቢ ያደረገ መሆን እንዳለበት ስምምነት መደረሱን ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ቃል ኪዳን የሰው ጉልበትን የሚጠቀሙ ስራዎች ላይ ማተኮርና ክህሎትን በቴክኖሎጂ ማጎልበት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 የተቀመጡ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ከንግግር ባለፈ የተግባር እርምጃ መውሰድ ያስችላልም ብለዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ቃል ኪዳን በፊት ኢትዮጵያ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ከፍተኛ የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችሉበትን ብሔራዊ መርሃ ግብር ገቢራዊ ማድረጓን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review