ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት እንደሚደግፍ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ተናገሩ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት እንደሚደግፍ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ተናገሩ

AMN- ግንቦት 28/2017 ዓ. ም

ኢትዮጵያ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የአሜሪካ መንግስት እንደሚደግፍ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ አስታወቁ፡፡

ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያስመዘገበች መሆኗንም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ አሜሪካ ከወሳኝ አጋሯ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ እንደምትሰራም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢትዮጵያ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እንደምትሰራ በአጽንኦት መግለጻቸው ይታወሳል።

ኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄዋ እንዲመለስ በሰላማዊ፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ሰጥቶ በመቀበል መርህ እንደምትሰራ በተደጋጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያስታወቁት ጉዳይ ነው።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በፈጣን ኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ትገኛለች።

ሀገሪቱ ሰፊ የህዝብ ቁጥር ያላት እና ፈጣን ኢኮኖሚ እያስመዘገበች እንደምትገኝ ያወሱት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ይህ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እንደሚቀጥልም ትንበያ መኖሩን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመገንባት ያላትን ህልም ለማሳካት የባህር በር አማራጯን ማስፋት ወሳኝ መሆኑን ጠቁመው፤ በሰላማዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት የምታደርገውን ጥረት የአሜሪካ መንግስት የሚደግፈው መሆኑንም አረጋግጠዋል።

አምባሳደር ማሲንጋ እንዳብራሩት፤ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላም እና ፀጥታ ለማረጋገጥ አሜሪካ ከወሳኝ አጋሯ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ትሰራለች።

ኢትዮጵያ ቀጣናው ወደ መረጋጋትና ሰላም እንዲመለስ አስተዋጽኦ እያደረገች መሆኑን አመልክተው፤ ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ መስራት አሜሪካ በአፍሪካ ቀንድ ያላት ጠንካራ አቋም መሆኑን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ግዙፍ ብቻ ሳትሆን አቅም እና ተጽዕኖ ያላት ሀገር ነች ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፤ በቀጣናው መረጋጋትና ሰላም ለማስፈን ሀገራቱ በጋራ እንደሚሰሩ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review