ኢትዮጵያ የተመድን የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት አጀንዳውን በባለቤትነት ይዛ እየተገበረች መሆኗ ተገለጸ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የተመድን የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት አጀንዳውን በባለቤትነት ይዛ እየተገበረች መሆኗ ተገለጸ

AMN- ሰኔ 02/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የ2030 ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አጀንዳውን በባለቤትነት በመያዝ እየተገበረች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የ2030 የዘላቂ ልማት አጀንዳ ትግበራ ሀገራዊ የፈቃደኝነት የዘላቂ ልማት ግቦች አፈጻጸም ሪፖርት ዝግጅትን መገምገማቸውን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እነዚህን የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ተጨባጭ ሀገራዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ አጀንዳውን በባለቤትነት በመያዝ እየተገበረች መሆኑንም አመላክተዋል።

ለዚህም ከ10 ዓመቱ ሀገራዊ መሪ የልማት ዕቅድ፣ ከሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም እንዲሁም ከሶስት ዓመቱ የልማት እና የኢንቨትመንት ዕቅድ ጋር በማስተሳሰር በርካታ ስራዎችን እያከናወነች እንደምትገኝ አንስተዋል።

የለውጡ መንግሥት ሁለንተናዊና አካታች ብልጽግናን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ባለው መልኩ በርካታ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ እና የመልካም አስተዳደር ሪፎርሞችን ማካሄዱንም ጠቁመዋል።

እነዚህ የሪፎርም ስራዎች የዘላቂ ልማት ግቦችን ከመተግበር አንጻር የበለጠ አቅም እንደፈጠሩም አንስተዋል።

የተገኙ ሥኬቶችን ለማጠናከርና ቀሪ ሥራዎችን ለመፈጸም የፌደራል ተቋማት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ከእቅድ እስከ ትግበራ ወጥ፣ የሚለካና ግልፅ የመረጃ ሥርዓትን መዘርጋት ለነገ የማይባል ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ማህበረሰቡን ያሳተፈ የሀብት ማሰባሰብን ማጠናከር እንዲሁም በፈቃደኝነት ላይ ለተመሠረተው የግምገማ ሪፖርቱ በሳይንሳዊ ጥናት የተመሰረተ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል።

ሦስተኛው የዘላቂ ልማት ግቦች ሀገራዊ የፈቃደኝነት ግምገማ ሪፖርቱ በገለልተኛ አካል መጠናቱ እንደሀገር የሚያበረታታ ሥራ መሥራታችንን የሚያሳይ እንዲሁም ለቀጣይ እንድንተጋ ትምህርት የወሰድንበት ነውም ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review