ኢትዮጵያ የአንካራውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ቁርጠኛ ነች- አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ

AMN-ታህሣሥ 15/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የአንካራውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ለመተግበር ቁርጠኛ መሆኗን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።

በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ የተመራ ልዑክ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት እያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት እልባት ለመስጠት በተርክዬ አሸማጋይነት ታኅሣሥ 2/2017 ዓ.ም ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል።

በዚህም መሰረት የአንካራውን ስምምነት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሐመድ ፈርመውታል።

የአንካራውን ስምምነት በማፅናት በሁለቱ ሀገሮች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በሶማሊያ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል።

የሶማሊያ የልዑካን ቡድን በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከተመራ ልዑክ ጋር ውይይት አድርጓል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንዳሉት፤ የሶማሊያ ልዑክ የስራ ጉብኝት ከአንካራው ስምምነት በኋላ የመጀመሪያው ነው።

የአንካራውን ስምምነት ገቢራዊ በማድረግ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ቀጣይነት ያለው ውይይት እናደርጋለን ብለዋል።

የሶማሊያ ሰላም የኢትዮጵያ ሰላም መሆኑን ገልጸው፥ ሽብርተኝነትን በመከላከል በቀጣናው ሰላም ለማስፈን ትብብራችን ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።

የሶማሊያ የውጭና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር ከወንድሜ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር ፍሬያማ ውይይት አድርገናል ብለዋል።

ከአንካራው ስምምነት በኋላ የመጀመሪያ ጉብኝታቸው መሆኑን ገልጸው፥ ስምምነቱን ገቢራዊ ለማድረግ የሚያስችል ውይይት ማድረጋቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review