ኢትዮጵያ የኢንተርፖልን ዓላማ ለማሳካት ቁርጠኛ ናት፡- ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል

AMN- ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የኢንተርፖልን ዓላማ ለማሳካት ቁርጠኛ ናት ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑካን ቡድን በእንግሊዝ ስኮትላንድ እየተካሄደ ካለው 92ኛው የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባኤ ጎን ለጎን ከድርጅቱ ኃላፊዎችና ከተለያዩ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር የሁለትዮሸ ውይይት አካሂዷል።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ከኢንተርፖል ፕሬዝዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናስርና በአሁኑ ጉባዔ አዲስ ከተመረጡት ዋና ፀሃፊ ቫልዴዚ ኡርኪዛ ጋር ተገናኝተው ባደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ የድርጅቱን ዓላማ ለማሳካት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ ዓመታት የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባኤን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ፍላጎት ስላላት የድርጅቱ ፕሬዝዳንት እና ዋና ፀሃፊው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጋብዘዋል።

ሁለቱም ኃላፊዎችም ግብዣውን ተቀብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ልዑኩ በእንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው እና በኢትዮጵያ የሬድ ፎክሰ ማዕከል ከፍቶ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በትብብር እየሰራ ከሚገኘው National Crime Agency (NCA) ኃላፊዎች ጋርም ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እና በኤጀንሲው መካከል ስላለው ግንኙነት እና የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም በቀጠናው ስላሉ የወንጀል ስጋቶች ተወያይቷል።

ልዑካን ቡድኑ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየሰጠች ስላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግኖ በቀጣይ የተጀመረው የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲሰፋ እና በሌሎች ዘርፎችም ትብብርና አጋርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ የተዘጋጀው የመግባቢያ ሰነድ በቀጣይ ጥቂት ወራት በአዲስ አበባ ለመፈራረም ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

ከዚህም በሻገር ልዑካን ቡድኑ ከቻይና፣ ከዩናይትድ አረብ ኤምሬት፣ ከናሚብያ፣ ከኮሎምቢያ፣ ከኳታር፣ ከምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ቢሮ ኃላፊ እና ከተለያዩ ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ውይይት አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተተገበረ ስላለው ሪፎርም፣ ከአባል ሀገራቱ የፖሊስ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠል እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሁለትዮሸ ውይይት አድርጎ የጋራ ስምምነት ላይ መድረሱን ከፌደራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

#Addisababa

#Ethiopia

ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!

https://linktr.ee/AddisMediaNetwork

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review