AMN – የካቲት 18/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል እንድትሆን እየሰራ ያለው የቴክኒክ ኮሚቴ የዝግጅት ስራውን መገምገሙን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ሚኒስትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት ፣ ለአምስተኛው የዓለም የንግድ ድርጅት የስራ ቡድን የቴክኒክ ኮሚቴው የመጨረሻ ዝግጅት ስብሰባ ላይ በመገኘት የስራ አቅጣጫ እንደሰጡ አመላክተዋል፡፡
የቴክኒክ ኮሚቴው በቢሺፍቱ ከተማ በማካሄድ ላይ በሚገኘው ዝግጅት እ.አ.አ በ2026 በካሜሮን በሚካሄደው የአለም ንግድ ድርጅት 14ኛው የሚኒስትሮች ኮንፍረንስ ላይ የኢትዮጵያን አባልነት ለማሳካት ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡
በዚህ መሰረት በከፍተኛ ሞራል፣ የሃገር ፍቅርና የሙያ ብቃት ዝግጅት ማድረግና ለተደራዳሪ ቡድኑ አቅም መሆን እንዳለባቸውም ገልጸናል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡
የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጎዚ ኦኮንጆ በቅርቡ በሃገራችን በነበራቸው ቆይታ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል።