
AMN-ግንቦት 18/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የጀመረችው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ዘላቂና አካታች የፋይናንስና የኢንሹራንስ ስርዓትን ለመገንባት ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል።
51ኛውን የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ዓመታዊ ኮንፈረንስና ጠቅላላ ጉባኤ ”የክፍያ ሚዛንን ማስተካከል፦ የአፍሪካ የእዳ ጫና፣ የሃገራት እዳ የኢንሹራንስ ድርጅቶች ላይ እንዴት ተጽዕኖ ያሳድራል? መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ፤ በኢትዮጵያ እየተከናወነ ያለው የኢኮኖሚ ሪፎርም የግሉን ዘርፍ የሚያበረታታና ኢንቨስትመንትን የሚስብ መሆኑን ገልፀዋል።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው የፋይናንስ ዘርፉን ህግ በማሻሻል በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ የሚያመጡ የአሠራሮች መዘርጋታቸውንም አስገንዝበዋል።
በኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በፋይናንስ ዘርፉ የተሰሩ ተግባራት የኢንሹራንስ ዘርፉን ዕድገት የሚያጎለብቱ ከመሆናቸውም ባሻገር ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ ሰፊ አበርክቶ እንዳላቸው አብራርተዋል።

የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ኢትዮጵያን ጨምሮ በ47 የአፍሪካ እና በ12 ከክፍለ አህጉሩ ውጭ ባሉ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ 400 አባላት ያሉት ሲሆን የአፍሪካን የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ለማስፋፋት እና ለማሳደግ እ.ኤ.አ በ1972 የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የዚሁ ድርጅት አባል ነው፡፡
በይታያል አጥናፉ