
AMN-ህዳር 4/2017 ዓ.ም
ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን እና የባለፈውን አመት የCOP28 ኃላፊነቶቿን በሶስት ሥራዎች እየተገበረች ትገኛለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኀበራዊ ትስስር ገፃቸው ፣ #COP29 እየተካሄደ ባለበት ወቅት ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ቀውስ ጉዳይን መፍትሔ ለማስገኘት የሚከናወኑ ተግባራት ፋይናስን ኢላማ ከማድረግ ባሻገር ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን የሚያራምዱ የጋራ ግን በነፍስወከፍ የተለዩ ኃላፊነቶችን ብሎም ታሪካዊ ተጠያቂነትን የሚያጠይቁ መሆን እንዳለባቸው አፅንዖት መስጠቷን ጠቁመዋል።
ግልፅነት ያለቸው የአየር ንብረት የገንዘብ ድጋፍ ብያኔዎች እድገትን እንደ አፍሪካ ባሉ አካባቢዎች የሚገኙ ዝቅተኛ የልማት መጠን ያላቸው ሀገራትን በተጨባጭ ለመከታተል አስፈላጊ ናቸውም ብለዋል።
ኢትዮጵያ የፓሪስ ስምምነትን እና የባለፈውን አመት የCOP28 ኃላፊነቶቿን በሶስት ሥራዎች እየተገበረች እንደምትገኝ አስታውቀዋል።
ቀዳሚው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ 40 ቢሊዮን ችግኞችን በመትከል የደን ሽፋን ከነበረበት በ6 በመቶ እንዲያድግ ማድረጉን አንስተዋል።
ሌላው በ2015 የምርት እጥረትን ወደ ትርፍ ምርት የለወጠው በመስኖ የለማ ስንዴ መርሃግብር መሆኑን የገለፁ ሲሆን በታዳሽ የኃይል ምንጭ የታገዙ የእግረኛ መንገዶች ያሏቸው እና የኤሌትሪክ ተሽከርካሪዎች የቀረቡባቸው ዘላቂና አረንጓዴ ከተሞችን የፈጠሩ ለአየርንብረት ጥበቃ ምቹ የሆኑ ዘመናዊ የከተማ ልማት ፕሮጀክቶች ሌላዎቹ ሥራዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።