ኢትዮጵያ ግብጽ ከምታመርተው የስንዴ ምርት በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ምርት እንደምታመርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ግብጽ ከምታመርተው የስንዴ ምርት በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ምርት እንደምታመርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ
  • Post category:ልማት

AMN- ግንቦት 29/2017 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ስንዴ አምራች ሀገር ብቻ ሳትሆን፣ በአፍሪካ ሁለተኛ የስንዴ አምራች ከሆነችዉ ግብጽ ሶስት እጥፍ ምርት እንደምታመርት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፣ ኢትዮጵያ ግብጽ ከምታመርተው የስንዴ ምርት በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ምርት እንደምታመርት ተናግረዋል፡፡

ያልተደመረ አቅም፣ እውቀት እና ሃብት ይዘን የምናስበውን ብልጽግና ማረጋገጥ እንችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ የቆላማ አካባቢ ሃብታችንን እና አቅማችንን ማወቅ ይገባናል ብለዋል፡፡

በሀገሪቱ ከሚገኙ ቆላማ አካባቢዎች ደቡብ ኦሞን እንደምሳሌ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በአካባቢዉ ያለው የውሃ እና የመሬት ሀብት ለረጅም ጊዜ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

መንግስት የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ ለቆላማ አካባቢዎች በሰጠው ትኩረት ትልቅ የውሃ አቅም ያለው 145 ኪሎ ሜትር የውሃ ካናል መሰራቱን አንስተዋል፡፡

አፋር፣ ሱማሌ እና ቦረናን በመሰሉ ቆላማ አካባቢዎችም ከፍተኛ የልማት አቅም መኖሩንና ሀገሪቱ ያላትን ቆላማ መሬት የማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቆላማ መሬቶችን ማልማት ዜጎች በልማት ውስጥ ያላቸውን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ተደርጓልም ብለዋል፡፡

የምግብ ሉአላዊነትን ለማረጋገጥ በተሰራው ስራ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመጀመሪያዋ ስንዴ አምራች ሀገር መሆኗን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በአፍሪካ ሁለተኛ የስንዴ አምራች ከሆነችው ግብጽ ሶስት እጥፍ ምርት እንደምታመርትም ገልፀዋል፡፡

የተገኘውን ለውጥ ማጥላላት እና ማራከስ መሞከር አይቻልም፣ በስንዴ ልማት የተገኘው ለውጥ በተጨባጭ የሚታይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ቴክኖሎጂንም ጥቅም ላይ በማዋል አሁን ላይ በሀገሪቱ ምን ያክል መሬት እንደታረሰ ማወቅ እንደሚቻል እና ምን ያክል ምርት መሰብሰብ እንደሚቻል መገመት እንደሚቻልም አብራርተዋል፡፡

በወንድምአገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review