ኢትዮ ቴሌኮም ለ47 ሺህ 377 ዜጎች እና ድርጅቶች 10.7 ሚሊየን አክሲዮኖችን በተከፈለ 3.2 ቢሊየን ብር መሸጡን ይፋ አድርጓል።
ኢትዮ ቴሌኮም ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለኢትዮጵውያን ለሽያጭ ያቀረበውን የ10 በመቶ ድርሻ አፈጻጻም በሚመለከት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።
መንግስት አካታች፣ ዘላቂነት ያለውና ተወዳዳሪ የሆነ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ለግሉ ዘርፍ በሰጠው እድል፣ ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶውን ድርሻ ጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ለዜጎች መሸጥ መጀመሩ ይታወሳል።
ዜጎች ካፒታል ገበያ ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተደረገው የኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ድርሻ ሺያጭ መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ በፍትሀዊነት መከናወኑን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ ተናግረዋል።
ከጥቅምት 6 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመጀመሪያው ዙር እያንዳንዳቸው 300 ብር ዋጋ ያላቸው 10.7 ሚሊየን አክሲዮኖች መሸጣቸውን ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።
አንድ ዜጋ ወይም ድርጅት መግዛት ከተፈቀደለት ከ33 አክሲዮን ጀምሮ እስከ 3 ሺህ 333 አክሲዮኖች ድረስ ለ121 ቀናት የአክሲዮን ሺያጩ ስለመከናወኑ ሥራ አስፈፃሚዋ አስታውቀዋል።
በቀጣይ ለባለድርሻዎች የአክሲዮን ድልድል የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል።
መተማመንን እና ግልፅነትን ለመፍጠር 3.2 ቢሊየን ብሩ ብሎክ በሆነ አካውንት መቀመጡ የተገለፀ ሲሆን፣ የቀሪ አክሲዮኖች ሺያጭ ህግና ስርዓትን ተከትለው እንደሚከናወኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልፀዋል።
በንጉሱ በቃሉ