የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዩት ከከርሰ ምድር አስከ ስፔስ ድረስ የሚሸፍን የመረጃ ስርዓት የገነባ እንደሆነና የከርሰ ምድር ውሀ ሀብትታችን ምን ላይ እንዳለ እና የመሬታችንን ሀብት እንድንለይ አስችሎናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስቲትዮት ከተመሰረተ አጭር ጊዜው ቢሆንም፣ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሆነም ተናግረዋል።
ለአብነት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የውሀ ሙሌቱ ከተጀመረበት እስካሁኑ ሰዓት ድረስ ያለው መረጃ በዚህ ተቋም አማካኝነት ተመዝግቦ እንደሚገኝም ነው የጠቆሙት።
ተቋሙ የመሬት አያያዝ ስርዓታችን ላይ የራሱን ሚና እየተጫወተ መሆኑን ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መሬቶች እያንዳንዳቸው በመለየት መሬቱ የማን ነው፣ በቦታው ላይ ምን እየተከናወነ ነው፣ የሚለውን ለመለየት እንዲሁም በመሸጥ በመለወጥ ሂደት ውስጥ ያለውን አሰራር መንግስት እንዲያውቀው ተቋሙ የሰራው ስራ ትልቅ እንደሆነም ነው ገልጸዋል።
የመሬት ካርታ ከማተም ባለፈ ተቋሙ ዲጂታል ካርታን በማስተዋወቅ እና ከዛም አልፎ ካርታን በመተግበሪያ ጭምር ይዞ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡
እነዚህ ተግባራት በተቋሙ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ያህል ተስፋ ሰጪ እንደሆነ የሚያሳዩ መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
በታምራት ቢሻው