የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ተመልክቷል።
አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የሪፎርም ሥራዎችን በመሥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ እተሻሻለ ተመራጭ የመረጃ ምንጭ መሆን መቻሉን ተቋሙ ለቋሚ ኮሚቴው ባቀረበው የዘጠኝ ወራት የሥራ ክንውን ላይ አመላክቷል።
ይዘት ጥራት እና ፈጠራ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ የሚገኘው ሚዲያው፣ ከኮሪደር ልማት ሥራዎች ጋር ተያይዞ የመጣውን የሥራ ባህል ለውጥ ለማስረፅም በስፋት እየሰራ ይገኛል።
በየት ደረሰ የዘገባ ሽፍኑ የአገልግሎት ቅኝት ማድረግ፣ ህዝብና መንግስትን የሚያቀራርቡና በችግሮች ዙርያ መፍትሄ የሚያመላክቱ ዋርካ፣ አገልጋዩ እና ጠረጴዛን የመሳሰሉ ጠንካራ ይዘቶቹ ሚዲያው የህዝብ መሆኑን ያሳየበት ነው ተብሏል።

በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በስፋት እየሰራ ሲሆን፣ ትምህርት በቴሌቪዥን መጀመሩም የትውልድ ድምፅ ከሆነ ሚዲያ የሚጠበቅ መሆኑ ተገልጿል።
በየወቅቱ የሚኖሩ አዳዲስ መረጃዎችን፣ በከተማዋ የሚከበሩ ሃይማኖታዊ እና ሀገራዊ በዓላትን በቀጥታ ስርጭት ለህዝብ ማድረስ መቻሉም ተገልጿል።
ከወቅቱ ጋር ተወዳዳሪነትን የሚጨምር የዲጂታል ሚዲያ፣ የቴሌቪዥን ዜና ዝግጅት እና አቀራረብ ማሻሻያ ሥራዎች መከናወናቸም ተብራርቷል።
ቀደም ሲል ያጋጠመው የሬዲዮ ሥርጭት ችግር መቆራረጥ መቀረፉ፣ አዲስ የዲጂታል አርካይቭ ሲስተም ተግባራዊ መደረጉን ተቋሙ በሪፖርቱ አመላክቷል።
በጠንካራ የይዘት ሥራዎቹ ከ6 ተቋማት እውቅናዎችን ማግኘት መቻሉም ተገልጿል።

በአሁኑ ሰዓት የሚዲያው የዘጠኝ ወር አጠቃላይ አፈፃፀም 97 ነጥብ 6 በመቶ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የሚዲያው ተወዳዳሪነት ደረጃም ከቀዳሚዎቹ ተርታ ላይ መሆኑን ሪፖርቱ አመልክቷል ።
ከሪፖርቱም በኋላ አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ በይዘት ሥራዎቹ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሚዲያ ተቋም እየሆነ መምጣቱን የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የፍትህና መልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ ተናግረዋል።
በተለይም የኮሪደር ልማት ገፅታን በማስተዋወቅ ረገድ አበርክቶው ተኪ የለውም ሲሉ ነው ሰብሳቢው የገለፁት።
ይህም ዓለም የአዲስ አበባን ለውጥ እንዲገነዘብ አስችሏል ነው ያሉት።
የመጣው ውጤት የተቋሙ አመራር በቅንጅት እና ትኩረቱን ሥራ ላይ በማድረጉ የመጣ መሆኑን አመላካች እንደሆነም አንስተዋል።
ሚዲያው በትክክልም የትውልድ ድምፅ እንደሆነ እና የአዲስ አበባን ህዝብ በትክክል እያገለገለ እንደሚገኝም ሰብሳቢው ተናግረዋል።
አስፈፃሚ አካላት የህዝብን ድምፅ የሚያደምጡበት እንደ አገልጋዩ፣ ዋርካ እና ጠረጴዛን የመሰሉ ሥራዎቹ አበረታች ናቸውም ብለዋል።
በማሬ ቃጦ