የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ የሰራተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ26ኛ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ3ኛ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ ተከብሯል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታጠቀ ተቋም እንዲሆን የተለያዩ ሪፎርሞች መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
እሳት እና ድንገተኛ አደጋን በዘላቂነት መከላከል የሚቻለው በልማት ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ልማት የማከናወን ስራ ዜጎችን ከአደጋ መከላከል ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል።
የድንገተኛ አደጋ ሰራተኞች ትልቅ ክብር እንደሚገባቸው እና ከተማ አስተዳደሩ በሁሉም መስክ ድጋፍ እንደሚያደርግም ከንቲባ አዳነች ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አህመድ መሃመድ፣ ኮሚሽኑ አደጋን የተመለከቱ የማስተማር እና የማስገንዘብ ስራዎች እያከናወነ እንዳለ ገልጸው፣ በፍጥነት አደጋ ከተከሰተበት ስፍራ በመድረስ አፋጣኝ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ የ24 ሰዓት የአምቡላንስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ እና የተቀላጠፈ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የኮሚሽኑ ሰራተኞች የመዲናዋን ነዋሪዎች ህይወት እና ንብረት ለመታደግ የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውም ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዶክተር ሽፈራው ተክለማሪያም በበኩላቸው በራስ አቅም እራስን ለማገልገል ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል፤ ለዚህም በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው ስራ ማሳያ ነው ብለዋል።
መዲናዋ በፍጥነት እያስመዘገበችው ያለችው ዕድገት ከዚህ በፊት ሲያጋጥም የነበረውን የአደጋ ስጋት እየቀነሰው እንደሚገኝ የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስራ አስኪያጅ ኢንጅነር ወንድሙ ሴታ ናቸው፡፡
በሀብታሙ ሙለታ