AMN – የካቲት 22/2017 ዓ.ም
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳን ለ129ኛውን የአድዋ የድል ቀን በዓል አደረሳችሁ፤ አደረሰን በማለት መልካም ምኞቱን ገለጿል፡፡
የምክር ቤቱ የእንኳን አደርሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
አድዋ! እውነት ነው! እናት አባቶቻችን ውድ የሆነውን ሕይወት ዋጋ የከፈሉት ለእውነት ነው!፡፡ “ያለነፃነት ከመኖር ነፃነት ይዞ መሞት ይሻላል ብለው ነው፡፡”
ኢትዮጵያ በታሪኳ የሌላ ሀገር ሉዓላዊ ግዛት በኃይል ወራ አታቅም፤ባሕር ተሻግራም የማንንም ሀገር ድንበር ተጋፍታም አታውቅም፡፡ ይልቁንም በየዘመናቱ ድንበሯን ጥሰው ነፃነቷን በኃይል ለመውሰድ በተደጋጋሚ የመጡ የውጭ ወራሪ ኃይሎችን በጀግኖች ልጆቾቿ የተባበረ ክንድ መክታ አሳፍራ መልሳለች፡፡ በጀግኖች ልጆቿ በተከፈለ ውድ የሕይወት መስዋዕትነት ጭምር ለብዙ ሺህ ዓመታት ነፃነቷን አስጠብቃ ታፍራና ተከብራ ቆይታለች፡፡
የአድዋ ጦርነት ለነፃነትና ለሉዓላዊነት የተደረገ ጦርነት ነው፡፡ ለእውነት ተዘምቶ ‘እውነት ያሸነፈበት’ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን እውነትን ስለሚይዙ ሁሌም አሸናፊ ናቸው፡፡ ለዚህም ነው ‘እውነት ያሸንፋል’፤ ‘እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል’ የሚሉና የመሳሰሉ ብሂሎች በኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተለመዱት፡፡ አድዋ ላይ የተከፈለው መስዋዕትነት ለእውነትና ለነፃነት ነው፡፡ እውነትን ክደው ገፍተው የመጡብንን ጠላቶች ገፍተን አሳፍረን መልሰናቸዋል፡፡
የአድዋ ድል የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ደማቅ የታሪክ የተፃፈበት ነው፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ አብዛኛው የአፍሪካ አህጉር በአውሮፓውያን ኃያላን ሀገራት ቅኝ ግዛት ስር በወደቀበት ዘመን በቀይ ባህር ዳርቻ መነሻ አደርጎ ግዛቱን ሲስፋፋ የቆየው የኢጣሊያ ወራሪ ኃይል የኢትዮጵያን ነፃነት ለማጥፋት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ድንበር ጥሶ በመግባት በወርሃ የካቲት 1888 ዓ.ም የኃይል ወረራ በኢትዮጵያ ላይ ሊፈፅም ችሏል፡፡
የአድዋ ድል የኢትዮጵያዊያን ነፃነት ከማስጠበቅ አልፎ በዘመነ ኢምፔሪያሊዝም በቅኝ ግዛት ቀንበር ስር ወድቀው በጭቆና ሲሰቃዩ የቆዩ ጥቁር ሕዝቦች ለነፃነታቸው እንዲነሱ አነሳስቷል፤
ለፓን አፍሪካኒዚም መጠንሰስ ምክንያት ሆኗል፡፡
ስለሆነም የአድዋ ድል የመላው የጥቁር ህዝቦች የድል ታሪክ ሆኖ ሲዘከር ቆይቷል፤ በዘንድሮ ዓመትም ለ129ኛ ጊዜ እየተዘከረ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ወቅታዊ ፍላጎት ከድህነትና ኋላቀርነት መውጣትና ብልፅግናን ማረጋገጥ ነው፡፡ ይህ እውን የሚሆነው በመንግሥት ፍላጎትና ጥረት ብቻ አይደለም፡፡ ሁላችንም እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማህበረሰብ የበኩላችንን ድርሻ በአግባቡ መወጣት ስንችል ነው፡፡ እናት አባቶቻችን በየዘመናቸው ጊዜው የጠየቃቸውን ውድ የሆነውን የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል ጭምር ነፃና ሉዓላዊት ሀገር በክብር አስረክበውናል፡፡
እኛ የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን የእናት አባቶቻችንን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ የልማት አርበኛ ሆነን የራሳችንን ታሪክ በደማቁ ልንፅፍ ይገባል፡፡ድህነትንና ኋላቀርነትን ለማጣፋትና በሁሉም መስክ የኢትዮጵያን ብልፅግና ለማረጋገጥ በተሰማራንባቸው ሥራ መስኮች ሁሉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝግብ ተግተን ልንሰራ ይገባል፡፡
ብሔራዊ አንድነታችንንና አብሮነታችንን የሚፈታተኑ እሳቤዎችንንና ተግባራትን አምርረን በመታገል ለብሔራዊ መግባባት፣ ለሀገር ክብርና ዘላቂ ጥቅም መረጋገጥ በተባበረ ክንድ በአንድነት ልንቆም ይገባል፡፡
በድጋሚ እንኳን ለ129ኛውን የአድዋ የድል ቀን በዓል አደረሳችሁ ! አደረሰን!
የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የካቲት 22 ቀን ፣ 2017 ዓ.ም