በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት እንደመንግስት በሀገር አቀፍ ደረጃ የአገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም ለማስተግበር በከፍተኛ ቁርጠኝነት በመንቀሳቀስ ላይ እንገኛለን ብለዋል።
የሪፎርሙ ዓላማ በከፍተኛ ትጋት፣ ቁርጠኝነትና ፍጥነት ይሳካ ዘንድ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች ተሳታፊ የሆኑበት መድረክ በአፍሪካ ሊደርሺፕ አካዳሚ “ልህቀት በሰው ተኮር አገልግሎት” በሚል መሪ ሀሳብ የአቅም ግንባታ መድረክ እያካሄድን ሲሆን በመድረኩም ገንቢ ሀሳቦች እየተገኙበት ነው።
ሪፎርሙ በዋናነት 5 ዋና ዋና መነሻ ጉዳዮች ያሉትና እነዚህንም ትኩረት በማድረግ፦ ተገልጋዩን የህብረተሰብ ክፍል በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ የሚያደርግ፣ አመራሩንም ሆነ ፈፃሚ አካሉን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሲሆን በጥልቅ ምክክር እየዳበረ እና እየበለጸገ የሚሄድ የትግበራ ሂደትን ያነገበ ነው።
በመነሻነት ከተወሰዱ ጉዳዮች በቀደምትነት የሚጠቀሰው የ10 አመት መሪ የልማት እቅድን እና 2ኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራን በስኬት ለመፈፀም የሚያስችል መሆኑ ተጠቃሽ ነው። የመንግስትን የመፈፀም አቅም በመገንባት ቀልጣፋ፣ አስተማማኝና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት አሰጣጥን ለመተግበር በር ከፋችም ነው።
እንዲሁም ሂደቱ የመደመር እሳቤን እና ፕራግማቲክ አቅጣጫን መሰረት ያደረገ እሳቤን ያገናዘበም ነው። ይህም በመሆኑ ነባር የሆኑ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል፣ ስህተቶችን እያረቀ የሚሄድ ብሎም በሁሉም አካባቢ የሚገኙ ጥንካሬዎችን ደምሮ ለመጠቀም የሚያስችል መርህን የሚከተል መሆኑ የትግበራውን ትሩፋት አጓጊ አድርጎታል።
ከዚህም ባሻገር ሰው ተኮር እሳቤን መሰረት ያደረገ እና በሲቪል ሰርቪሱ ዙሪያ ያሉ አካላትን በተለይም ተገልጋዩን፣ ሰራተኛውን እና አመራሩን ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል እንቅስቃሴ ተደርጎም የተቀረጸ ነው። ሂደቱም ግልጽነት፣ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ፣ ፈጠራ እና ፍጥነትን ለማሳደግ፣ የተገልጋዩን ጥቅም የሚያስከብር የትግበራ አንጓዎች ያሉት ነው።
በተጨማሪም ሪፎርሙ ከህገመንግስቱ እና ከፌደራል ስርዓቱ ጋር የተጣጣመ ሲሆን የአንድነታችን መገለጫ የሆኑ እሴቶችን በተጨባጭ ውጤት እንዲያመጡ የሚያደርግ አላስፈላጊ የሆኑ የኢፍትሀዊነት ቅርፊቶችን የሚገፍ፣ በፌደራል እና በክልል መንግስታት የጋራ ጥረት ተግባራዊ ይደረጋል ተብሎ ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል።
በጥቅሉ ጠንካራ እና ቅቡልነት ያላቸው ተቋማትን ለመገንባት እድል የሚሰጥ በመሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለግቦቹ መሳካት እና ለትግበራ ሂደቱ መሳለጥ ገንቢ ሚናቸውን እንዲወጡ በዚህ አጋጣሚ አደራ ለማለት እወዳለሁ – በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ