እንደ ንብ የታተሩ ተምሳሌቶች

You are currently viewing እንደ ንብ የታተሩ ተምሳሌቶች

የሌማት ትሩፋት ብዙዎቹን በንብ ማነብ፣ በዶሮ እርባታ፣ በእንቁላል እና በወተት ምርት ተጠቃሚ እያደረገ ስለመሆኑ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በከተማ ደረጃ የከተማ ግብርና አይቻልም የተባለውን አስተሳሰብ የሰበሩ በርካታ ተጠቃሚዎች ይገኛሉ፡፡ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍልም በየካ እና በጉለሌ ክፍለ ከተሞች በንብ ማነብ ስራ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ግለሰቦችን ተሞክሮ እንደሚከተለው አቅርባለች፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 10 ነዋሪ የሆኑት አቶ መስፍን ተሾመ በባህላዊ ቀፎዎች ንብ ማነብ ከጀመሩ በርካታ ዓመታትን ማስቆጠራቸውን ጠቁመው፣ በተጠናከረና በዘመናዊ መንገድ መስራት የጀመሩት ግን በሌማት ትሩፋት ንቅናቄው አማካኝነት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ በተለይ ከአራት አመት ወዲህ የተሻለ ውጤት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡

አቶ መስፍን በሶስት ባህላዊ ቀፎዎች ስራቸውን እንደጀመሩና አሁን ላይ 11 ዘመናዊ እና ሶስት ባህላዊ ቀፎዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል። የማር ምርት ተጠቃሚነታቸው እንደወቅቱ ሁኔታ እንደሚለያይ ገልጸው፣ በዓመት ሁለትና ሶስት ጊዜ ማር በመቁረጥ ለገበያ ያቀርባሉ። በተያዘው ዓመት በጥቅምት ወር ብቻ 46 ኪሎ ግራም ማር ማግኘት ችለዋል፡፡ አንድ ኪሎ ግራም 700 እስከ 800 ብር ሂሳብ በመሸጥ ወደ 38 ሺህ ብር ገቢ አግኝተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በሚያዝያ እና በግንቦት ወር በማር ሽያጭ 28 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

ንብ ማነብ ከማሩ በላይ ስራው እንደሚያስደስታቸው የሚገልጹት አቶ መስፍን፣ ማንኛውም ሰው ባለው ትንሽ ክፍት ቦታ ንብ በማነብ በማር ምርት ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

ቀፎዎች እና ቦታቸው በንፅህና ከተያዘ ለንቦች ስለሚመቻቸው የተሻለ ውጤት እንደሚሰጡ ገልጸው፣ ሁሌም ቦታቸውን ዝግጁ እና ንጹህ በማድረግ ንቦችን መንከባከብ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ቀፎዎችን በጭስ አጥኖ ዝግጁ አድርጎ በመያዝ እንዲሁም አበባዎችን በመትከል ንቦችን በማማለል መማረክ እንደሚቻልም ጠቁመዋል፡፡

በንብ ማነብ ስራ ለወጣቶች የስራ እድል እንደፈጠሩ የሚናገሩት አቶ መስፍን በቀጣይ ስራውን የበለጠ አስፋፍተው ለሌሎች ተጨማሪ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ወይዘሮ ብርሃን በርሄ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 9 ነዋሪ ሲሆኑ 20 ዘመናዊ ቀፎዎች እንዳሏቸው ገልፀዋል። በዚህም ባለፈው ዓመት 400 ኪሎ ግራም የማር ምርት አግኝተዋል፡፡ ለንቦች የሚሆን ልዩ ልዩ የአበባ ዛፎችን በመትከል በማር ምርት የተሻለ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በስራቸው ለአራት ግለሰቦች የስራ እድል የፈጠሩት ወ/ሮ ብርሃን ከማር ምርት ሽያጭ በሚያገኙት ገቢ ቤተሰባቸውን በተሻለ ደረጃ በማኖር ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ነዋሪ የሆኑት አቶ ጥጋቡ ሽታነህ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ በንብ ማነብ ስራ መሰማራታቸውን አስታውሰው፣ በአሁኑ ጊዜ 30 ዘመናዊ ቀፎዎች እንዳሏቸው ገልፀዋል፡፡ ከተማ ላይ ንብ ማነብ አይቻልም የሚለውን አስተሳሰብ የቀየሩት አቶ ጥጋቡ፣  ባለፈው አመት በግንቦት ወር ብቻ 25 ኪሎ ግራም ምርት አግኝተዋል፡፡

ቀፎ ብቻ በማስቀመጥ በዓመት የማር ምርት ተጠቃሚ መሆን እንደማይቻል አቶ ጥጋቡ ገልጸው፣ የንብ መንጋውን ጠብቆ በመያዝና ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በዓመት ጥራትና ብዛት ያለው የማር ምርት ማግኘት ይቻላል ብለዋል፡፡ ንቦች ልክ እንደ ልጆች ሁሉ እንክብካቤ ይፈልጋሉ የሚሉት አቶ ጥጋቡ ለንቦች የሚያስፈልጉ አበቦችና ውሐ እንዲሁም ሌሎች ግብዓቶች ከተሟሉ እንዲሁም እንክብካቤ ከተደረገላቸው የማር ምርት እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

በንብ ማነብ የማር ምርት ተጠቃሚ ለመሆን ቅድሚያ የራስ ተነሳሽነት ወሳኝነት አለው የሚሉት አቶ ጥጋቡ፣ በተጨማሪም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ውጤታማ መሆን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ በዚህ ረገድ እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ በተለይ የዘመናዊ ቀፎ አቅርቦትና ሌሎች ተያያዥ ግብዓቶች ውጤታማነታቸውን እንዳላቀው ገልፀዋል፡፡

በየካ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ልማት ጽህፈት ቤት የእንስሳት ሃብት ልማት ቡድን መሪ አቶ አለምሰገድ ሞገስ በክፍለ ከተማው ሰፊ የሆነ የንብ ሃብት መኖሩን ጠቁመው፣ ነዋሪዎቹ በንብ ማነብ በመሳተፍ ተጠቃሚ እየሆኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡  በክፍለ ከተማው 307 ነዋሪዎች በንብ ማነብ ተሳታፊ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ከእነዚህ ውስጥ 42 ማህበራት እና 267 ደግሞ ግለሰብ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አቶ አለምሰገድ የንብ ሃብት ለነዋሪዎች ህይወት መሻሻል ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ ዘርፉ ከዘመናዊ ቀፎ እና ቀላል ቴክኖሎጂ ያለፈ ሰፊ ጉልበት እና ተጨማሪ ግብዓት የማይጠይቅ በመሆኑ ሁሉም በዘርፉ በመሳተፍ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ዘርፉ ተጨማሪ ግብዓት አቅርቦት የማይጠይቅ እና ሰዎች ሳይጨናነቁ እየተዝናኑ የሚሰሩት በመሆኑ ዘርፉን ልዩ ያደርገዋልም ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት ለንብ ማነብ ንቅናቄና ተሳትፎ የራሱ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል። ነዋሪዎች በፊት ከገበያ በውድ ዋጋ ይገዙት የነበረውን የማር ምርት አሁን በራሳቸው ጓሮ በማምረት ፍጆታቸውን እንዲሸፍኑ አስችሏል ብለዋል፡፡

ክፍለ ከተማው ለንብ ሃብት ተስማሚ የአግሮኢኮሎጂ ከባቢ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ በመሆኑም የየካ ተራራ እና የኮተቤ አካባቢ ዙሪያ በርካታ ነዋሪዎች በንብ ማነብ ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

በጥቅምት፣ በህዳር እንዲሁም በሰኔ ወራት አካባቢ የማር ምርት እንደሚሰበሰብ ገልጸው፣ እነዚህን ወራት መሰረት ያደረጉ ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ ለንብ ማነብ ግብዓት የሚሆን የመገልገያ ቁሳቁስ፣ ልዩ ልዩ አልባሳት እንዲሁም የህብረንብ ግብዓት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ለተጠቃሚዎቹ ይህን ለማሟላት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ንብ ማነብ አሁን እየተለመደ መምጣቱን የሚገልጹት አቶ አለምሰገድ በከተማ በህንጻዎች፣ በክፍት ቦታዎች ንብ የማነብ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ገጠር ላይ ብቻ ሳይሆን ከተማ ላይ ንብ በማነብ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከአሁኑ የተሻለ የማር ምርት ለማግኘት የአካባቢን ስነ-ምህዳር ማሻሻልና መጠበቅ፣ የሰብል፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትና ምርታማነትን እንዲሁም የተለያዩ የእጽዋቶች ዝርያዎች በማሳደግ ለንብ ርባታው አመቺ ከባቢ መፍጠር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ 

በአዲስ አበባ ከተማ የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ኮሚሽን የእንስሳት ልማት የንብ እርባታ ባለሙያ አቶ ቢኒያም አድማሱ፣ በከተማዋ በንብ ማነብ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቁመው፣ በከተማዋ ከ2 ሺህ 393 በላይ ነባር ተጠቃሚዎች መኖራቸውን ገልፀዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት 964 ቶን የማር ምርት ለማምረት ታቅዶ 722 ቶን ማር ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በንብ ማነብ ስራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፤ የሚገኘው የምርት መጠንም አድጓል፤ በዚህ አመት በከተማዋ 430 ሺህ 320 ኪሎ ግራም የማር ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል

በዚህ አመት ከነባር አምራቾች በተጨማሪ 1 ሺህ 478 ግለሰቦች በንብ ማነብ መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በከተማዋ ከ3 ሺህ በላይ ተጠቃሚዎች በንብ እርባታ በማር ምርት ተሳታፊ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ተስማሚ የአየር ጸባይ ያላት እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች በስፋት በመሰራታቸው ለንብ እርባታ ስራ አመቺ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የከተማ ግብርና ከጀመረ ወዲህ በከተማዋ የንብ እርባታ ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን አቶ ቢኒያም ጠቁመው፣ ለዘርፉ ውጤታማነት የዘመናዊ ቀፎ የግብዓት አቅርቦት እንዲሁም ከወረዳ እስከ ማዕከል ድረስ የስልጠናና የሙያዊ ድጋፍ  በመስጠት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በከተማዋ በዚህ አመት 430 ሺህ 320 ኪሎ ግራም የማር ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡

በይግለጡ ጓዴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review