ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸዉ ቆይታ ከድህረ እዉነት ዘመን ጋር ተያይዞ ማህበረሰቡ ሃሰተኛ መረጃዎችን የማጣራት ዝንባሌ እየፈጠረ መምጣቱን ገልጸዋል።
በለዉጡ ጊዜ በሃገሪቱ የነበረዉ የቴሌቭዥን ብዛት 4 ሚሊዮን ብቻ እንደነበረ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ 20 ሚሊዮን ቴሌቭዥን መኖሩንና ባለፉት ስድስትና ሰባት አመታት የቴሌቭዥን ብዛት በሶስትና አራት እጥፍ ማደጉን ገልጸዋል፡፡
በነዚሁ የለዉጥ አመታት ከአሁን በፊት ያልነበሩ 160 ሚዲያዎች መጨመራቸዉን ተናግረዋል።
ከተወሰኑ አመታት በፊት ኢትዮጵያ ዉስጥ ቴሌቪዥን የማየት እድሉ አልነበረም: አሁን ላይ ግን የቴሌቪዥኑና የሚዲያዉ ቁጥር ጨምሯል ሲሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የሚዲያ ቋንቋዎች ብዛት ስልሳ መድረሱን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበረሰብ ሬድዮዎች ጭምር በነዚህ ቋንቋዎች መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ተደራሽ እንደሚያደርጉና በዘርፉ እድገት መታየቱን ጠቁመዋል፡፡
ከሚዲያ አፈጣጠርና አመጣጥ ጋር በተያያዘም በአለም ላይ ገለልተኛ የሚባል ሚዲያ የለም ፣ ሚዲያዎች ሲቋቋሙ የራሳቸዉ ተልእኮ አላቸዉ ሁሉንም ሚዲያ ከጀርባ የሚነዳዉ ሃሳብ አለ ብለዋል፡፡
ለሚዲያዎች ድጋፍ የሚያደርጉ አካላትም የራሳቸዉ አላማ እንዳላቸው በመጠቆም።
ባለፉት ሁለትና ሶስት አመታት በሃገሪቱ የታየዉ የሚዲያ እድገት ወደ ደህረ እዉነት አለም ከቶናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ላይ በርካታ የፈጠራ ሃሰተኛ መረጃዎች ይሰማሉ ብለዋል፡፡
ተጨባጭ ያልሆኑ መረጃዎችን የሚያሰራጩ መኖራቸዉንና ተጠያቂነት አለመኖሩንም በመግለጽ።
የማይገቡና የተሳሳቱ መረጃዎች ቢሰራጩም ህብረተሰቡ የሚሰማዉን መረጃ ሁሉ አምኖ ከመቀበል ረገድ ለዉጥ መኖሩን ጠቁመዋል።
በተለይ ማህበረሰቡ በሃሰተኛ መረጃ ምክንያት ከገጠመዉ ፍዳና መከራ የተነሳ መረጃዎችን አጣርቶ መስማት መጀመሩን አንስተዋል።
አሁን ያለንበት ዘመን የድህረ እዉነት ዘመን ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሃሰተኛ መረጃዎች አሉ: የማጣራት ዝንባሌዉ እየተፈጠረ ነዉ ቢሆንም ግን አላለቀም ብለዋል።
ለዚህም መረጃ የማጥራትና ተጠያቂነትን የማስፈን ስራ ሊጠናከር ይገባል ብለዋል።
ማህበራዊ ሚዲያዎች የበርካታ ዉሸቶች ምንጭ መሆናቸዉን በመገንዘብ ወደ እዉነት የሚያመሩ ሚዲዎችን ለይቶ መከታተል: ሲያበላሹ የሚጠየቁበትን በአሰራር ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በወንድማገኝ አሰፋ