AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም
ከለውጡ ወዲህ በአገሪቱ የዘመነ እና የሰለጠነ የዴሞክራሲ ባህል እንዲዳብር የሚያስችሉ ትልልቅ ርምጃዎች መወሰዳቸውን የብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ገለጹ፡፡
አቶ ሞገስ ባልቻ የብልጽግና ፓርቲ ቅድመ ጉባኤን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ ፣ ባለፉት ዓመታት በአጠቃላይ የፖለቲካ ምህዳሩን በመክፈት ለሀሳብ እኩልነት እና ለሀሳብ ልዕልና ቦታ ተሰጥቶ በተደረገ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን አውስተዋል፡፡
በዚህም በሀሳብ ሞግቶ እና አሸንፎ በህዝብ ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ላይ በትኩረት መሰራቱን አስረድተዋል፡፡
አዲስ እና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲዳብር ለማድረግ ቀድሞ ታፍኖ የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር የመክፈት ስራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡
ዲሞክራሲውን በተፈለገው ሁኔታ ማሳደግ የሚያስችለውን የፖለቲካ ምህዳር በማስፋት አሳሪ ህጎችን የመፈተሽ እና የማረም ርምጃዎች መወሰዳቸውንም ጠቅሰዋል ፡፡
በሀገሪቱ ጠንካራ የዲሞክራሲ ባህል እንዲገነባ የዲሞክራሲውን መሰረት ሊያሳድጉ የሚችሉ የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ስራ መከናወኑንም አብራርተዋል።
እነዚህ ጉዳዮች ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ በመሆናቸው ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
በዚህም የምርጫ ቦርድ ፤ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና ሚዲያው ወሳኝ በመሆናቸው በእነዚህ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ስራ እየተሰራ ነው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሚፈለገውን የዘመነ እና የሰለጠነ የዲሞክራሲ ባህል ለመገንባት ትልልቅ ርምጃዎች ተወስደዋልም ብለዋል
በዚህም ዜጎች የመሰላቸውን ሀሳብ የሚያነሱበት፤ የመደራጀት መብት እና በውጪ ተሰደው የነበሩ የፖለቲካ ሀይሎች ወደ ሀገር ገብተው ሰላማዊ ትግል የሚያደርጉበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩንም አንስተዋል፡፡
በዚህ ረገድ በመንግስት በኩል የፖለቲካ ቁርጠኝነት የታየበት መሆኑን ተከትሎ በተለይም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ከፍተኛ ለውጥ የታየበት የተለያዩ ሀሳቦች መንጸባረቃቸውን ብሎም ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለአንድ አገራዊ ዓላማ አብሮ የመስራት፤ የመቀራረብ እና በመንግስት አስፈጻሚነት እንዲካተቱ ማድረግ አዲስ የፖለቲካ ባህል መፍጠር መቻሉን አውስተዋል፡፡
በመሆኑም ወቅቱ በሀይል ላይ ከተመሰረተ ወደ ሰለጠነ የፖለቲካ ባህል የተሸጋገርንበት እና ይህንን ይበልጥ እያሳደጉ መሄድ እንደሚጠበቅም አስረድተዋል፡፡
በሰለሞን በቀለ