AMN – ጥር 20/2017 ዓ.ም
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ገቢራዊ የተደረጉ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ሀገራዊ ኢኮኖሚውን ከቀውስ መታደግ ማስቻላቸውን የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በኢኮኖሚው መስክ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎችና የተገኙ ስኬቶች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ከለውጡ በፊት የነበረው አሰራር ኢኮኖሚውን በአግባቡ መምራት ባለመቻሉ በከፋ ችግር ውስጥ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከለውጡ በፊት የመንግሥት ገቢ የተቀዛቀዘበት፣ የዕዳ ጫናው የናረበት፣ የባንኮች የማበደር አቅም ያሽቆለቆለበት በአጠቃላይ የፋይናንስ ስርዓቱ ጤናማ ያልሆነበት ወቅት እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ይሁን እንጂ ከለውጡ በኋላ በተወሰዱ የፖሊሲ ማሻሻያዎች ችግሮችን ተቋቁሞ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ጤናማ ኢኮኖሚ በመገንባት ከቀውስ መታደግ ተችሏል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የፊሲካልና ሞኒቴሪ ፖሊሲ እርምጃዎች፣ የውጭ ምንዛሬ ግኝት ማሻሻያዎች፣ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድጉ አሰራሮች ገቢራዊ መደረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢኮኖሚው በውስን ዘርፎች ላይ የተንጠለጠለ እንደነበር በማንሳት፤ ከለውጡ በኋላ ለብዝሃ ኢኮኖሚ የተሰጠው ትኩረት ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል፡፡
ባንኮች በኢኮኖሚው ላይ የላቀ አበርክቶ እንዲኖራቸው የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በመንግሥት የተወሰዱ የፖሊሲ ርምጃዎች የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ገቢያቸውን ጨምሮ በተለያዩ መስኮች አፈጻጸማቸውን በማሻሻል ኢኮኖሚው እንዲያገግም ገንቢ ሚና ተወጥቷል ብለዋል፡፡
የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን መደረጉ የትይዩ ዋጋው ከመደበኛው ጋር እንዲቀራረብ ከማስቻሉም በላይ ሕገ ወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዲቀንስ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር ነዳጅን ጨምሮ በመሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ድጎማ መደረጉን ገልጸው፤ መንግሥት ባደረገው ሁሉን አቀፍ ጥረት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡
የፖሊሲ ርምጃዎች ከልማት አጋሮችና አበዳሪ ተቋማት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በማስገኘታቸው ኢኮኖሚው እንዲረጋጋት ጉልህ ድርሻ መወጣታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የገጠሙትን ፈተናዎች ተቋቁሞ ቀጣይነት ያለው እድገት እያስመዘገበ መሆኑንም ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡