በታይላንድ ባንኮክ ከተማ በመንገድ ጽዳት ስራ ትተዳደር የነበረች አንዲት ወጣት ሴት በአንድ ጀምበር ለሞዴሊንግ ሥራ መታጨቷ ብዙዎችን እያነጋገረ ነው።
አንድ በተፈጥሮ ውበቷ የተደነቀ ሲሚዮን ሬዢኮቭ የተባለ ሩሲያዊ የካሜራ ባለሙያ ያነሳትን ፎቶ በቲክቶክ ገጹ ላይ ማጋራቱን ተከትሎ ነው ወጣቷ የብዙዎች ዓይን ውስጥ መግባት የቻለችው፡፡
ሁለት ልጆቿን ለብቻዋ የምታሳድገው የ28 ዓመቷ ናፓጂት ሚን ሳምቡንሴት የተባለችው ወጣት፣ ሩሲያዊው የካሜራ ባለሙያ ከርቀት ፎቶ በሚያነሳት ወቅት፣ ኑሮዋን ለማሸነፍ የተለመደ የእለት ስራዋን እያከናወነች ነበር።
ሩሲያዊው የካሜራ ባለሞያ በድንገት ያያት እና በተፈጥሮ ውበቷ የተደነቀባትን ወጣት ፎቶ ሲያነሳት ፈፅማ አላየችውም፡፡
በተለያየ ሁኔታ ከርቀት ያነሳትን ፎቶ ቀረብ ብሎ በማሳየትም የተፈጥሮ ውበቷን አድንቆ የሄደው የካሜራ ባለሙያ፣ ያነሳትን ፎቶዎች በስልኩ በማቀናበር እንደዋዛ በቲክቶክ ገጹ ላይ ይለጥፈዋል፡፡
ይሁን እንጂ የለጠፈው ምስል በፍጥነት የብዙዎችን ቀልብ የሳበ ሲሆን፣ ብዙ ሰዎችም የወጣቷን ውበት በማድነቅ ስለእርሷ ይበልጥ ማወቅ እንደሚፈልጉ መግለጽ ጀመሩ፡፡
ናፓጂት ሳምቡንሴት በታይላንድ በሚገኙ መገናኛ ብዙሃን ቀርባ ባደረገችው ቃለ ምልልስ፣ ለአንድ ዓመት ያህል የመንገድ ጽዳት ስራ ስትሰራ እንደነበረች እና በስራዋም በጣም ደስተኛ እንደነበረች ተናግራለች።
ሬዢኮቭ በሰራው ሥራ እና በምላሹም ብዙዎች በዚህ ፍጥነት እንደዚህ አይነት አድናቆት መቸራቸውን ፈፅማ ያልጠበቀችው መሆኑን በመግለጽ፣ ነገር ግን ያ ገና ጅማሬ እንደነበር ገልፃለች።
በብዙዎች በጎረፈላት አድናቆት ዝነኛ የሆነችው ሚን፣ ቻቻይ ፔንፋፒቻርት ከተባለው ታዋቂ የታይላንድ የስነ ውበት ተቋም፣ በፊልም ሥራ እንድትሳተፍ ዕድል አግኝታለች፡፡
እንዲሁም ድርጅቱ የሚያመርታቸውን የመዋቢያ ቁሳቁሶችን እና በሌሎች የማስታወቂያ ኤጀንሲዎች አስተዋዋቂ ሞዴል በመሆን እየተመረጠች ሲሆን፣ በቅርቡም በአዲሱ ስራዋ ላይ ትኩረት ለማድረግ ስትል የጽዳት ሥራዋን ማቆሟን እንደገለጸች ኦዲቲ ሴንትራል ዘግቧል፡፡
የ28 ዓመቷ ወጣት በአሁኑ ሰዓት በታይላንድ ውስጥ በጣም ከሚወራላቸው እና ከሚነገርላቸው ሰዎች አንዷ ለመሆን እንደበቃችም መረጃው ያሳያል።
በወርቅነህ አቢዮ