ከማጀት ተርፎ ወደ መንደር

የከተማ ግብርና በሰፊም ይሁን በአነስተኛ ቦታ፣ ለምግብነትና ለገቢ ምንጭነት ሊውሉ የሚችሉ እፅዋትን የማልማት፣ እንስሳትን የማርባት፣ የግብርና ምርት ውጤቶችን ከማምረት ባሻገር የማቀነባበር እና ለተጠቃሚዎች የማቅረብ ስራን የሚያካትት ነው፡፡ ብዙዎች በዚህ ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ በመሆን ላይ ናቸው። ከእነዚህ ትጉህ፣ መስራት ከማይታክታቸው፣ ስራን ከማይንቁ፣ ከትንሽ ተነስተው ትልቅ ደረጃ ለመድረስ ከሚታትሩ ጠንካራ እናቶች መካከል ወይዘሮ ዘሃራ ከማል አንዷ ናቸው፡፡

ወይዘሮዋ የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ የተወለዱት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሲሆን አዲስ አበባን ቤቴ ብለው መኖር ከጀመሩ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኗቸዋል፡፡ “መስራት ያስከብራል፤ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ የፈለገ ሰው በተሰማራበት የስራ መስክ ውጤታማ የሚሆነው ብዙ ፈተናዎችን አልፎ ነው፡፡” የሚሉት ወይዘሮዋ ባለቤታቸውን በሞቱ ካጡ ጀምሮ በችርቻሮ (ጉሊት) ንግድ ተሰማርተው በሚያገኙት ገቢ ታማሚ እናትና ወንድማቸውን እንዲሁም ሦስት ልጆቻቸውን ሲያስተዳድሩ ቆይተዋል፡፡ አሁንም በስራው ቀጥለውበታል፡፡

በጉሊት ስራ ብቻ ኑሮን መግፋት ያልቻሉት እኚህ እናት፤ በ2017 በጀት ዓመት መጀመሪያ ሐምሌ ላይ 50 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን በመግዛት ወደ ከተማ ግብርና ስራ እንደገቡ ይናገራሉ፡፡ 

የዝግጅት ክፍላችን በቤታቸው በተገኘበት ወቅት ያገኛቸው ለዶሮዎቻቸው ምግብና ውሃ እያቀረቡ ሲመግቡ ነበር፡፡ ዶሮዎቹም መጋቢያቸውን ሲያዩ እናታቸው እንደመጣችላቸው ህፃናት ድምፃቸውን ሲያሰሙ ተመልክተናል። ወይዘሮ ዘሃራ የጉሊት ስራ እየሰሩ በቆጠቧት ሽርፍራፊ ሳንቲም ነው 50 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን ለእርባታ የገዙት፡፡ በሚሰሩት ስራም ደስተኛ ናቸው። በኢኮኖሚ ማደግ ህልማቸው በመሆኑና እንስሳት በሚያረባ ቤተሰብ ማደጋቸው የከተማ ግብርና ስራውን ለማስፋት ቆርጠው እንዲነሱ አደረጋቸው። ከሚሰሩት የከተማ ግብርና ስራ በሚያገኙት ገቢ እቁብ በመግባት ተጨማሪ 1 ሺህ ዶሮዎችን ገዝተው በመጨመር በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 50 ዶሮዎች አሏቸው፡፡

በከተማ ግብርና ላይ የተሰማሩት ወ/ሮ ዘሃራ ከማል ዶሮዎችን በመንከባከብ ላይ

“ወደ ዶሮ እርባታ እንድገባ ያደረገኝ አንዱና ዋነኛው ምክንያት ችግር ነው፡፡ ችግሬ ገንዘብ ብቻ አልነበረም፤ ልጄ ተምሮ ስራ ማጣትም ጭምር እንጂ፡፡ ‘ችግር ብልሃትን ይወልዳል’ እንደሚባለው ጠንክሬ እንድሰራ እነዚህ ነገሮች መነሳሳት ፈጠሩልኝ” የሚሉት ወይዘሮዋ፤ የልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 በጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷቸው፣ በቀን ሦስት ጊዜ ለእያንዳንዱ ዶሮ 120 ግራም ምግብ በመመገብ፣ እንዳይታመሙ መድሃኒት በመስጠት እንክብካቤና ክትትል እንደሚያደርጉላቸው ነው የነገሩን፡፡

ዶሮዎችን ለመንከባከብ ሲገቡ በጫማቸውና በእጃቸው ዶሮዎችን የሚጎዳ በሽታ ይዘው እንዳይገቡ ውጭ ላይ የእጅ ሳኒታይዘርና ጫማን ንፁህ የሚያደርግ ኬሚካል ይጠቀማሉ። የሚጠጡበትንና የሚመገቡበትን እቃ በንፅህና መያዝ፣ ትናንት ከዛሬ ያላቸውን እንቅስቃሴ በመከታተል የተሻለ የእንቁላል ምርት እንዲሰጡ እያደረጉ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ዘሃራ፤ አሁን ልጃቸው ስራ አጥ በነበረበት ወቅት የነበረባቸው ጭንቀት ተወግዷል። ስራዬ ብሎ ዶሮዎችን በመንከባከብ ያግዛቸዋል፡፡ ‘እየሰራሁ ነው’ የሚል የህሊና እረፍት አግኝቷል። ስራ መስራት ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የሚያስገኘው ሥነ ምግባርንም ያንፃል። ይህንንም የራሴ ልጅ ምስክር ነው ይላሉ፡፡  

ወይዘሮዋ ስራ በጀመሩባቸው ሁለት ወራት ውስጥ በቀን እስከ 100 እንቁላል ያገኙ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት በቀን እስከ 450 እንቁላል ያገኛሉ። እንቁላል መጣል ያልጀመሩ ዶሮዎች መጣል ሲጀምሩ ከዚህም በላይ ማግኘት እንደሚችሉ ይናገራሉ፡

ስራ ወዳድነት ከቤተሰብ ይወረሳል፤ እናትና አባቴ አሁን ለምሰራው ስራ መሰረቶቼ ናቸው። ከእንስሳት ጋር ያደገ ለእንስሳት ያለው ፍቅር ይጨምራል፡፡ እኔም እነሱ የሚሰሩትን ስራ እያየሁ ነው ያደግኩት። ላሞችንና ዶሮዎችንም ስንከባከብ ቆይቻለሁ፡፡ አሁን ለምሰራው ስራም መሰረት ሆኖኛል ይላሉ ወይዘሮ ዘሃራ፡፡

በመዲናዋ የተጀመረው የከተማ ግብርና ነዋሪዎች ከጓሮ ትኩስ እንቁላል፣ አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የወትት ተዋፅኦዎችን እንዲያገኙ እያደረገ ነው፡፡ እኔም እንቁላሉን በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆንኩ ነው፡፡ ከዋጋም አንፃር ከ1 ብር እስከ ሁለት ብር ድረስ ልዩነት በቅናሽ ነው የማቀርበው፡፡ ገበያ ላይ ከ13 እስከ 14 ብር የሚሸጠው፤ እኔ በቅርብ ለሚገኘው ነዋሪ 12 ብር አቀርባለሁ፡፡

“ዶሮዎቹ እንቁላል መጣል ከጀመሩ ጀምሮ ቸግሮኝ አያውቅም፡፡ መኗቸውን ጉሊት ለመሸጥ ከማመጣው ሰላጣ፣ ጎመን እና ቆስጣ ላይ ጥቅም ላይ የማይውለውን ነው የምጠቀመው፡፡ ይህም እንቁላላቸው ጣፋጭ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ለመኖ የማወጣውንም ወጭ ቀንሶልኛል” ይላሉ፡፡

ወይዘሮዋ አሁን ላይ ከራሳቸውና ከልጃቸው ባለፈ ለሁለት ወጣቶች የስራ እድል ፈጥረዋል። ወደፊትም የእንቁላል ጣይ እና የስጋ ዶሮዎችን ቁጥር በማሳደግ፣ ስራቸውን በማስፋት የሚያገኙትን ገቢ የማሳደግ እቅድ እንዳላቸው ነግረውናል፡፡

ከእናቱ ጋር እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን መንከባከብ መጀመሩ ደስታን እንደፈጠረለት የሚናገረው ደግሞ የወይዘሮ ዘሃራ ልጅ ወጣት ነስረዲን ሬድዋን ነው፡፡ “በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በዲግሪ ተመርቄ ስራ አልነበረኝም። በዚህም የወደፊት ተስፋም ሆነ ሰርቶ የመለወጥ  ህልሜ ተሟጥጦ ነበር” የሚለው ወጣቱ፤ እናቱ 50 ዶሮዎችን ገዝተው አብሮ እንዲሰራ ሲያደርጉት የመኖር ተስፋውን “ሀ” ብሎ እንደጀመረ ይናገራል። የዶሮዎችን መኖ የማምጣትና የመመገብ እንዲሁም እንቁላል የሚወስዱ ደንበኞችን የማፈላለግ ስራዎችን በመስራት እናቱን በስራ እንደሚያግዛቸው ነው የነገረን፡፡

“ስራን ከትንሽ በመጀመር ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ ይህ ስራ ለእኔ መሰረቴ ነው። ስራ በማፈላለግና በመቆዘም ያሳለፍኩት ጊዜም እንዲቆጨኝ አድርጎኛል። በስራ ውጤታማ ለመሆን ዋናው የባለቤቱ አላማ ነው፡፡ መሰላልም ሲወጣ ከታች ተጀምሮ ነው፡፡ በሶስት ወራት ውስጥ ከ50 ዶሮዎች 1 ሺህ 50 ደርሰናል። ይህ ጅማሬያችን እንጂ ፍፃሜያችን አይደለም” የሚለው ወጣቱ፤ ወደፊትም የዶሮዎችን መጠን በመጨመር 10 ሺህ እንቁላሎችን ለማከፋፈልና እንደ እሱ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን የስራ እድል መፍጠር የወጣቱ የወደፊት ህልም ነው፡፡

አቶ አማኑኤል አስራት በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት የከተማ ግብርና እና የእንስሳት ጤና ቡድን መሪ ናቸው፡፡ የከተማ ግብርና ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆን የክትትልና ድጋፍ እያደረግን ነው፡፡ ለምሳሌ የዶሮ እርባታ ዘርፍን ብናነሳ፣ በዘርፉ ለተሰማሩት አንዲት ዶሮ ስድስት ጊዜ እንቁላል እንድትጥል፣ በቀን 120 ግራም ምግብ ማግኘት እንዳለባቸው፣ መድሃኒቶችን እንዴት እንደሚሰጣቸው ማሳወቅ፣ የህክምና አገልግሎት (ክትባት)፣ ምርጥ ዘሮችን ወይም ለእንቁላል የሚሆኑ ዶሮዎችን ከየት ማግኘት እንዳለባቸው በስልጠና እንዲያውቁ  ይደረጋል፡፡ በእፅዋትና እንስሳት እንክብካቤ ላይ ለተሰማሩትም ስራውን በምን መልኩ ማከናወን እንደሚችሉ ስልጠናዎች እንዲያገኙ እንደሚደረግ ገልፀዋል።

የከተማ ግብርና ውጤታማ ሲሆን ጥራቱን የጠበቀ እና ትኩስ ምርትን ለማህበረሰቡ ለማቅረብ ሚናው ከፍተኛ ነው። ማህበረሰቡም በተመጣጣኝ ዋጋ በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የአትክልትና የእንስሳት ምርቶች በብዛት እየቀረቡ ተጠቃሚ እየሆነ ይገኛል፡፡ ብዙም ያልተለመደው የዶሮ ስጋ ብዙዎች እየተመገቡት ነው፡፡ ይህም የሆነው ከወንድ የስጋ ዶሮዎች በተጨማሪ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች እንቁላል መጣላቸውን ሲያቆሙ ለስጋ ስለሚውሉ እንደሆነ አቶ አማኑኤል ይገልፃሉ፡፡

እንደ ወረዳ ስምንት የከተማ ግብርናን ውጤታማ በማድረግ ረገድ መልካም እድሎችና ፈተናዎች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ አማኑኤል፣ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በየቀጠናውና በየብሎኩ አመራሮች ተመድበው ግንዛቤ መፍጠራቸው፣ ማህበረሰቡም ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ መምጣቱ ጥሩ እድል ነው፡፡ የመኖ እንዲሁም የመስሪያ ቦታ ሼድ በሚፈለገው ልክ የማግኘት እድል አለመኖር እንደ ችግር የሚጠቀስ ነው፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ለሚመለከተው አካል ጥያቄዎችን ጠይቀን ምላሹን እየጠበቅን ነው ብለዋል፡፡  

በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት በከተማ ግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችንና የተገኙ ውጤቶችን በተመለከተ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ኮሚሽን የእንስሳት ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሌክስ ደመቀ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡ በሩብ ዓመቱ በተለያዩ የከተማ ግብርና ልማት ዘርፎች በተለይም በቤተሰብ ፍጆታ 33 ሺህ 222 ለማሳተፍ ታቅዶ  (አንድ ቤተሰብ ከእንስሳትም ይሁን ከእፅዋት ልማት   የሚያገኘውና   ለገበያ   ሳይሆን   ለራሱየሚጠቀመው) 14 ሺህ 367 እና በሥራ ዕድል ፈጠራ (ምርታቸውን ከራሳቸው አልፈው ለገበያ በማዋል የገቢ ምንጭ የሚያገኙበት) 1 ሺህ 330 በድምሩ 15 ሺህ 697 የከተማ ነዋሪዎች በከተማ ግብርና እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ይህም የእቅዱ 43 በመቶ ተሳክቷል። አፈፃፀሙም ከእቅዱ ዝቅ ያለበትም ባለፉት ሶስት ወራት በዋናነት በበጀት ዓመቱ የሚከናወኑ ሥራዎችን በትክክል የማቀድ እና አስፋላጊውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ የተሰራበት የዝግጅት ምዕራፍ ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

የከተማ ግብርና ስራ በኮሚሽኑ ብቻ የሚሰራ አይደለም፡፡ ስልጠና ሲያስፈልግ ከግብርና ሚኒስቴርና የምርመራ ማዕከላት እንዲሁም መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት ጋር በመሆን እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡ ከእነዚህ አካላት ጋር ባለፉት ሶስት ወራት በዋናነት በበጀት ዓመቱ የሚከናወኑ ሥራዎችን በትክክል የማቀድና የጋራ የማድረግ፤ አስፈላጊውንም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም የተገኘው ውጤት አበረታች መሆኑን ነው የነገሩን፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ታሳታፊዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ ኮሚሽኑ፣ በየደረጃው ባለው መዋቅሩ ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎች በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በመጀመሪያ የሚገጥማቸውን ፈተና የመለየትና የማወቅ ስራ ይሰራል፡፡ ከዚያም እንደችግሩ ሁኔታ የግብዓት አቅርቦት፣ የእርሻ ቦታ አያያዝ ጋር የሚገናኝ የድጋፍና ክትትል ስራ ሲሰራ ቆይቷል፤ ወደ ፊትም በልዩ ትኩረት እንደሚሰራበት አቶ አሌክስ አንስተዋል፡፡ 

የዝግጅት ክፍላችን በዘርፉ ተሰማርተው የሚሰሩ ግለሰቦችን አግኝቶ ባነጋገርንበት ወቅት የመኖ፣ የእንስሳት ህክምና እንዲሁም የመስሪያ ቦታ ችግሮች እንዳሉ ለተነሱት ጥያቄ ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ፤ የከተማ ግብርና ሥራ እየተሰራ የሚገኘው በከተማ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ዕድሎች እንዳሉት ሁሉ በርካታ ችግሮችም ይስተዋላሉ፡፡ በተለይም የመስሪያ ቦታና የመኖ አቅርቦት ጉዳይ ትልቁን ድርሻ ይይዛሉ። ኮሚሽኑ የመኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ወደ መኖ ማቀነባበር ሥራ የሚገቡ ግለሰቦች እና ማህበራት እንዲበራከቱ እየሰራ ነው፡፡ የግል ባለሃብቶችም ወደ ዘርፉ በመግባት በተመጣጣኝ ዋጋ የመኖ አቅርቦት ሥራን እንዲያቀርቡ እየሰራ ይገኛል። የመስሪያ ቦታ እጥረትን በተመለከተም፤ ችግሩን ለመቅረፍ ቴክኖሎጂን መጠቀም ግድ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በውስን ቦታዎች ላይ የግብርና ስራውን እንዴት ልንሰራ እንችላለን በሚል እፅዋትን የሽቅብ እርሻን (Vertical Farming) መጠቀም፣ በሌላ በኩልም ያለ አፈር እንዲመረት የማድረግ እንዲሁም በእንስሳትም ዶሮዎችን መሬት ላይ ከማድረግ ይልቅ ወደ ላይ ቆጥ በመስራት ብዙ ዶሮዎችን በትንሽ ቦታ ላይ ለማርባት የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች በስራ ላይ እንዲውሉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡

የከተማ ግብርና ዘርፍ ላይ ያሉ ተሳታፊዎች ወደፊት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማድረግ እና ዘርፉ እንዲያድግ ኮሚሽኑ ዘመናዊ የከተማ ግብርና አሰራር እንዲሰፋ ማድረግ በቴክኖሎጂ የተደገፈ ግብርና እንዲኖር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተማ በግብርናው ተጠቃሚ ልትሆን የምትችልበት ትልቅ አቅም አላት። ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረትም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተጨባጭ ውጤት መጥቷል። ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ የተገኘውን ውጤት በማስፋት የከተማውን ነዋሪ ተጠቃሚ ለማድረግ መረባረብ ያስፈልጋል እንላለን፡፡

በፋንታነሽ ተፈራ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review