• በከተማዋ በርካታ የልማት ስራዎች በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተከናወኑ ስለመሆኑም ተጠቁሟል
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተጀመረው የኮሪደር ልማትና የመልሶ ግንባታ ስራዎች ላይ ህዝቡ በሀሳብ፣ በጉልበትና ገንዘቡ እያደረገ ያለው ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የኮሪደር ልማቱ የከተማውን ገፅታ፣ ፅዳትና ውበት ብሎም አርንጎዴ ልማት በማስፋት ትልቅ ክስተት እንዲሆን ማድረጉ ብቻ ሳይሆን፣ በአጭር ጊዜ የመዲናዋን ገፅታ በተሻለ መቀየር እንደሚቻል ያረጋገጠ እና የአምበሳውን ድርሻ የሚወስደው ራሱ ህዝቡ ስለመሆኑም ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉ የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ከፍያለው ዘውዳለም ይናገራሉ፡፡
እንደ ከተማ የተመዘገቡ ለውጦች በግልፅ የሚታዩ መሆኑን የገለፁት የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው ለአብነትም በቅርቡ በተመሰረተው ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ እየታየ ያለው የተነቃቃ የህብረተሰብ ተሳትፎን በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በክፍለ ከተማው ውበትና አረንጓዴ ልማት ፅህፈት ቤት የተፋሰስና አረንጓዴ ልማት ስራዎች አስተባባሪ የሆኑት ትሁንዘር ታደሰ እንደሚሉት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት አከባቢን በማልማት ስራዎች ላይ የሚያደርጉት የነቃ ተሳትፎ እለት ከእለት እየተሻሻለ የመጣና የሚያስደንቅ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
በተለይ እንደከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማትን መሰረት በማድረግ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አድርጓል የሚሉት አስተባባሪዋ በመንግስት ወጪ ከተከናወኑ ዋና ዋና የኮሪደር ልማት ስራዎች በተጨማሪ በያዝነው በጀት ዓመት ብቻ ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበትና በሃሳብ ከ50 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በርካታ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የተለያዩ ተቋማትና ድርጅቶች ያሏቸው ባለሃብቶችና ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ባሉ ክፍት ቦታዎች ችግኝ ከመትከል ጀምሮ ፋውንቴኖችን በመስራትና ስፖት ላይቶችን በመትከል የተለያዩ የአረንጓዴ ልማት ስራዎችን እያከናወኑ ነው ብለው ለአካባቢያቸው ውበትና ድምቀት የሚሰጡ መብራቶችን ባደጉ ዛፎች ላይ ጭምር በማድረግ ከፍተኛ ተሳትፎ እያረጉ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
እንደከተማ በተቀመጠው ደረጃ መሰረት በክፍለ ከተማው የተለያዩ አከባቢዎች በመንገድ አካፋዮች እና መሀከል ላይ የሚታዩ መብራቶች እንዲሁም ከመኖሪያና ከስራ ቦታቸው በሃምሳ ሜትር ራድየስ አራት ማዕዘን በማድረግ አረንጓዴ የማልበስና በመብራት የማስዋብ እንዲሁም እያንዳንዱ ባለሃብት ከዋናው የኮሪደር ስራ ጋር ተያያዥና ተመሳሳይ በሆነ መንገድ አጥርና ህንፃዎችን የማስዋብ ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
እንደ ክፍለ ከተማ በራስ አቅም እስከአሁን የተከናወኑ ስራዎችን መዘርዘር ቢያስፈልግ የኮንዶሚኒየምና የማህበራት ግቢን ጨምሮ 23 ሄክታር መሬት የለማ ሲሆን ከዚህ ውስጥ አምስት ነጥብ አምስት ሄክታር የሚሆነው የመንገድ ዳርቻዎችና አካፋዮችን በአረንጓዴ ልማትና በመብራት የማስዋብ ስራዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ በህብረተሰብ ተሳትፎ ከለሙት መካከልም በለሚ ኩራ ወረዳ 10 በተለምዶ ፍየል ቤት ተብሎ ከሚጠራው እስከ ተባባሩት፣ ከተባበሩት ደግሞ ወደ ሀያት በሚወስደው መንገድ መሪን ይዞ በሁለቱም አቅጣጫ እስከ ደራርቱ አደባባይ እንዲሁም ወረዳ 3 ከዙሪያሽ ሞል አንስቶ እስከ ሀያት 49 በሚወስደው መንገድ፣ በወረዳ 2 ደግሞ እንደዚሁ ከጣፎ አደባባይ እስከ ደራርቱ አደባባይ ያሉት ስራዎች ተጠቃሽ ናቸው።
በእነዚህ ስራዎች ማህበረሰቡ በቡድንና በተናጥል ተሳትፎ ሲያደርግ እንደነበር የጠቀሱት አስተባባሪዋ በግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ የነበሩ 5 መቶ 55 የሚጠጉ በጎ አልሚዎች እና በርካቶች ደግሞ በጋራ ሲሳተፉ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ በልማት ስራዎቹ ህብረተሰቡ የሚያደርገው ንቁ ተሳትፎ ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጠቁመው ህበረተሰቡ ገንዘብ ማዋጣት ብቻ ሳይሆን በተቀመጠው ደረጃ መሰረት እራሱ ዲዛይን በማድረግ አጠቃላይ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በፅህፈት ቤቱ የተቀመጠው 20/80 ደረጃ ወይም 80 በመቶውን አረንጓዴ የማልበስ 20 በመቶው ደግሞ በፋውንቴኖችና በመብራቶች የማስዋብ ስራ መሆኑን ጠቅሰው ይህም በአግባቡ እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
የማህበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ከፍያለው እንደሚሉትም የህብረተሰቡ ተሳትፎ ከፍ ማለት በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች ምን ያህል እየጠቀሙት እንደሆነ ህብረተሰቡ በራሱ እየተረዳ መሆኑን ያመላክታል። ህብረተሰቡ በስፋት የሚሳተፍባቸው ስራዎች ከፍ እያሉ ሲመጡ እንደ ሀገር የምናስመዘግባቸው ልማቶች የበለጠ ዘላቂነት ይኖራቸዋል፡፡ በአዲስ አበባም ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህንን የሚያመላክት ነውም ብለዋል፡፡
ስራው የተጀመረ አከባቢ በህብረተሰቡ በኩል ብዙም መነቃቃት አልነበረም ያሉት አስተባበሪዋ በፅህፈት ቤቱ በኩል በተሰራው ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በተጠናቀቁ አካባቢዎች ያለው ድባብ ሳቢና ማራኪ መሆኑን የተመለከተው ማህበረሰቡ ልማቱ የኔ ነው በሚል ስሜት ያለማንም ቀስቃሽ በንቃት ተሳትፎ ማደረግ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
ክፍለ ከተማው በ2013 ዓመተ ምህረት በቅርቡ የተቋቋመ እንደመሆኑ በተቋቋመ የመጀመሪያውና ሁለተኛው ዓመት ጠንካራ የህብረተሰብ ተሳትፎ ባለመኖሩ በህብረተሰብ ተሳትፎ የሚሰራው ስራ ከሁለት እና አራት ሄክታር እንደማይበልጥ የሚያስታውሱት አስተባባሪዋ ከ2015 ዓመተ ምህረት ወዲህ ግን የተነቃቃ ስራ መሰራት መጀመሩን አስረድተዋል፡፡
በየወረዳው ታዋቂና ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ እንደ አርቲስት ሰራዊት ፍቅሬ ያሉ አስር ሰዎችን የልማት አንባሳደር አድርጎ በመሾም እንደዚሁም በክፍለ ከተማው የሚኖሩ ባለሃብቶች የልማቱ አካል እንዲሆኑ በመጋበዛቸው በተጨባጭ የሚታይ ለውጥ መጥቷል ባይ ናቸው፡፡
እንደዚሁም በፅህፈት ቤቱ ግንዛቤ የማስረፅ ዘርፍ ባለሙያዎች በበራሪ ወረቀት ቤት ለቤት በመሄድና በፅህፈት ቤቱ የማህበራዊ ትስስር ገፅ ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ስራ መሰራቱንም ነው የጠቆሙት፡፡ እንደአስተባባሪዋ አባባል አካባቢን ማልማት፣ መጠበቅና መንከባከብ የአንድ ጊዜ ስራ አይደለም ከዚህ አኳያ ህብረተሰሱ እንደክፍለ ከተማ እያደረገ ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል ብቻ ሳይሆን በህብረተሰብ ተሳትፎም ሆነ በመንግስት የተከናወኑ የውበትና አረንጓዴ ልማት ስራዎችን መጠበቅ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በክፍለ ከተማው የግንባታ ፍቃድና ቁጥጥር ፅህፈት ቤት የግንባታ ክትትል ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ወንድሜነህ እሸቱ በበኩላቸው እንደከተማ እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት መነሻ በማድረግ የህብረተሰቡ ተሳትፎ እየጎለበተ መምጣቱን ነው ያረጋገጡት፡፡
እንደእርሳቸው አባባል በ2016 እና 17 ዓመተ ምህረት ብቻ ከመንግስት በጀት ውጪ በራስ አቅም ወይም በህብረተሰብ ተሳትፎ በ 1ሺህ 862 ህንፃዎች የቀለም፣ የመብራት፣ የአርኬድና የመሳሰሉት የስታንዳርዳይዜሽን ስራዎች ተሰርተዋል።
እድሳት ከተደረገላቸው ህንፃዎች መካካል 827 የመኖሪያ ቤቶች ሲሆኑ 646 የንግድ ቤቶችና 323 መኖሪያና ንግድ በጋራ የሆኑ ህንፃች ሲሆኑ ከዚህ ውጪ አጥሮችንም የከተማ አስተዳዳሩ ባስቀመጠው ስታንዳርድ መሰረት 6 ሺህ 323 ነጥብ 76 ሜትር ጊዚያዊ እና 14 ሺህ 323 ነጥብ 76 ሜትር ቋሚ አጥር መሰራቱን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 6 ህንፃዎች ዋናውን ህንፃ ሳይነካ በስሩ የሰዎች መተላለፊያ (አርኬድ) የተከፈተላቸው ሲሆን 9 የሚጠጉ የኃይማኖት ተቋማትና 15 የመንግስት ቷቋማት በድምሩ 1 ሺህ 862 ግንባታዎች ላይ ወደ ስታንዳርድ የማምጣት ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት አቶ ወንድሜነህ ለእነዚህም በግለሰብ ደረጃ ከ1 ቢሊየን 748 ሚሊዮን 991 ሺህ ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልፀዋል፡፡
ከማስዋብ ስራዎች ጋር ተያይዞም 16 ሺህ 620 ግድግዳ ላይ የሚገጠሙ መብራቶች ወይም የወል ማወንት የተገጠሙ ሲሆን 10 ሺህ 895 ካሬ ሜትር ደግሞ ዶትፒክስል የሚባሉ በህንፃዎች ግድግዳ ላይ ወደ ላይና ወደ ታች የሚበሩ መብራቶች ተገጥመዋል፡፡
በተጨማሪም 18 በሚጠጉ በተለያዩ አደባባዮችና ድልድዮች 355 ነጥብ 03 ሜትር ካሬ የሚያክል የዲጂታል ስክሪኖች እንዲተከሉ እና የንግድ ተቋማት ማስታወቂያዎችን በራስ አቅም በስታንዳርዱ መሰረት እንዲቀይሩ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በክፍለ ከተማው በራስ አቅም የልማት ስራዎችን ሲያከናውኑ ከነበሩ ተቋማት በወረዳ አስር የሚገኘው ፋርማኪዮር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በመባል የሚታወቀው ፋብሪካ አንዱ ነው። በተቋሙ የሰው ሃብት አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት ወይዘሮ ቃልኪዳን ጌታቸው እንደሚሉት ተቋሙ ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ እንደከተማ የወጣውን ስታንዳርድ መሰረት በማድረግ የተቋሙን አጥር ግቢ በተወሰነ መልኩ ወደ ወስጥ ከማስገባት ጀምሮ የመሰረተ ልማት ማስተካከያ አድርጓል፡፡
ግቢዉን ማራኪና እይታን የሚስብ ለማድረግ በተቋሙ ግቢ ወደ አንድ ሺህ ችግኞችን ከመትከል ባሻገር ያሉ ክፍት ቦታዎችን አረንጎዴ ማልበስና በተለያዩ መብራቶች የማስዋብ፣ 12 የዘንባባ ዛፎች ደግሞ ከ 400 ሜትር በላይ የሚሆን መብራት እንዲለብሱ ተደርጓል ብለዋል፡፡
በተመሳሳይም ከተቋሙ ፊት ለፊት ባለ ክፍት ቦታ ላይ ከወረዳ በተሰጣቸው ዲዛይን መሰረት ፋውንቴን እያሰሩ እንደሆነ ያስታወሱት የሰው ሃይል ዳይሬክተሯ ከግቢው ውጪ ያለ የመንገድ ዳርቻና አካፋይም ግሪን የማድረግና ስፖት ላይቶችን በመትከል ድርጅቱ የልማቱ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ለወደፊት በሚከናወኑ ልማቶች ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደሚሆኑ ተናግረዋል፡፡
በሸዋርካብሽ ቦጋለ