የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ዋነኛ ማዕከል፣ የአፍሪካ መዲናና የዓለም የዲፕሎማሲ ከተማዋ በሆነችው አዲስ አበባ በርካታ የልማት ስራዎች ቀን ከሌት በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ ከተማዋ ስሟንና ደረጃዋን የምትመጥን እንድትሆን እየተከናወኑባት ከሚገኙ ፕሮጀክቶች መካከል የኮሪደር ልማት ተጠቃሽ ነው፡፡ የመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት በስኬት ተጠናቅቆ ሁለተኛው ዙር መጀመሩም ይታወሳል፡፡
“አዲስ አበባ የነበረችበት ሁኔታ ደረጃዋን የሚመጥን አይደለም” እንዳልነበረ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር) ይናገራየኮሪደር ልማት ብዙ ትሩፋት እንደሚያመጣላትም ያስረዳሉ፡፡ ነጥቡን ሲያብራሩም፣ “አንደኛው ትሩፋት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲቀላጠፉ የሚያግዝ መሆኑ ነው፡፡ ከተማዋ ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ የሚደረግባት፣ ሁሉንም የምታሳትፍ፣ ኢንቨስትመንት መሳብ የምትችል፣ የመኖሪያ፣ የንግድና የመዝናኛ ከተማ እንድትሆን ያስችላታል” ብለዋል፡፡

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሐሙስ በተካሄደው በ6ኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሲሰጡ፣ “በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፍትሃዊ ልማትን ለዜጎቻችን ያቀረብንበት ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ወቅት የኮሪደር ልማት ስራን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለፁት፣ የኮሪደር ልማት ማለት ኢትዮጵያን የሚመጥን ከተማ መገንባት ማለት ነው ብለው፣ እየተከናወነ ያለው ተግባር ከከተሜነት እድገት ጋር የተሳሳረ ልማት ነው። በኮሪደር ልማት ሰፋፊ መንገድ ከመስራት ባለፈ አዳጊዎች እግር ኳስ የሚጫወቱባቸውን የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እና የእግረኛ መንገዶች የተሰሩበት እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ከተማን በፕላን መምራት የግድ ነው። ከተማ በአግባቡ ከተመራ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የቱሪዝም፣ የመዝናኛ በጥቅሉ ምቹ የመኖሪያ ማዕከል ይሆናል። ይህን ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ የመከራና ስቃይ ቦታ ይሆናል ይላሉ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በከተማ ልማትና ምህንድስና ኮሌጅ የከተማ ዲዛይንና ፕላን ተባባሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ሊሬቦ (ዶ/ር)፡፡
አዲስ አበባ ከተመሰረተች በኋላ ለ49 ዓመታት ምንም ዓይነት ፕላን ሳይኖራት ነበር ስታድግ የነበረው ያሉት ዳንኤል (ዶ/ር)፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መንገድ ለመቀየስ የተሞከረው በ1900 ዓ.ም በአርመናዊ አርክቴክት ሙሴ ሚናስ አማካኝነት ነበር፡፡ ከ1928 የጣሊያን ወራረ በኋላ የጣሊያን አርክቴክቶች ፕላን በማውጣት ለመተግበር ሞክረዋል፡፡ ከዚያ በኋላ በየጊዜው በከተማዋ ዕድገት ለማምጣትና የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት መዋቅራዊ ፕላኖች ሲሰሩ ቆይተዋል። በአሁኑ ወቅትም አስረኛው ፕላን እየተተገበረ ይገኛል ሲሉ ያስረዳሉ፡፡
የኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማህበር ፕሬዝዳንት አርክቴክት ሀብታሙ ጌታቸው በበኩላቸው፣ የኮሪደር ልማት ዋና ዓላማ አንዱን አካባቢ ከሌላው ጋር ማገናኘት ነው፡፡ ከተማዋ ምን ዓይነት ገፅታ እንዳላት ሰው ላይ ተስሎ የሚቀር ምስል የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ መንገድ፣ መብራት፣ የእግረኛ፣ የሳይክል መንገዶች፣ የውሃ ፍሳሽ መስመሮች፣ የአረንጓዴ ቦታዎች፣ ባዶ ቦታዎች፣ ህንፃዎችን ጭምር አካትቶ የያዘ ነው የሚል ማብራሪያ ሰጥተዋል።የልማት ኮሪደር በመካከለኛው ምስራቅ፣ በአውሮፓ፣ በሩቅ ምስራቅ፣ ላቲን አሜሪካና በአፍሪካ የሚገኙ ከተሞች መልሰው የሚለሙበት፣ ቀድሞ የነበሩ ስህተቶች የሚታረሙበት ወይም የሚስተካከሉበት የከተማ ልማት ሞዴል እንደሆነ ዳንኤል (ዶ/ር) ይናገራሉ። በመንገድ ግራና ቀኝ ደረጃቸውን የጠበቁ የመኖሪያ፣ የንግድ፣ ቢሮዎችን ጨምሮ ሁሉንም አገልግሎቶች የያዘ፣ 24 ሰዓት አገልግሎት የሚሰጥና ዘላቂነት ያለው ከተማ የሚገነባበት የከተማ ልማት ነው፡፡
ዳንኤል (ዶ/ር) እንደሚሉት የኮሪደር ልማት የሚከናወንባቸው ቦታዎች የከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን የጀርባ አጥንቶች ናቸው። የዋና ዋና መንገዶች የደም ስሮች ናቸው። እነዚህ መስመሮች የመዝናኛ፣ የንግድና ሌሎች አገልግሎቶችን በመስጠት የተጨናነቁ አካባቢዎች እንደመሆናቸው መለወጣቸው በብዙ መልኩ የከተማዋን ችግር ይቀርፋሉ፡፡ አዲስ አበባን ስናይ አንዳንድ አካባቢዎች ቀን ላይ ሞቅ ደመቅ ያሉ ሆነው ማታ አስፈሪ ድባብ ያለባቸው ናቸው፡፡
በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት አዲስ አበባ 24 ሰዓት የንግድና የተለያዩ እንቅስቃሴዎች የሚከናወንባት ከተማ ትሆናለች፡፡ ሰው ቀንና ሌሊት ይሰራል፤ ኢንቨስትመንትን ይስባል። 24 ሰዓት እንቅስቃሴ ባለበት ከተማ ደግሞ ወንጀልም ይቀንሳል፡፡ ሰርቶ የሚኖርና ልማት ላይ የሚያተኩር ህዝብ ይፈጠራል ይላሉ ዳንኤል (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለምክር ቤቱ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፣ ሌላው አለም ከዘመናት በፊት ከተሞቻቸውን እንዳለሙ ጠቅሰው፣ እኛ ከአርባ አመታት በፊት ኮሪደርን ማልማት ነበረብን፡፡ ሌላውን አለም አይተን መቆጨት አለብን፡፡ ለዚህ ደግሞ ካለፈ በኋላ ከመቆዘም ይልቅ ዕድልና ጊዜን በአግባቡ መጠቀም አለብን፡፡ “እኔ ያልጋገርኩት እንጀራ አይውጣ እኔ ያልሰራሁት ወጥ ይረር ከሚል እሳቤ እንውጣ” ብለው የኮሪደር ልማትን አለም እያደነቀው እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
በመለሰ ተሰጋ