AMN – ጥር 10/2017 ዓ.ም
የጥምቀት በዓል በየዓመቱ ጥር 11 ቀን በታላቅ በድምቀት ይከበራል። በተመሳሳይ ሁኔታ ከበዓሉ በፊት (የጥምቀት ዋዜማ) የከተራ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሮ ይውላል።
“ከተራ” የሚለው ቃል “ከተረ፣ ከበበ ከሚለው የግዕዝ ግስ የወጣ ነው። ከተራ ፍቺውም “ውኃ መከተር፣ ወይም መገደብ” ማለት ነው።
በየዓመቱ ጥር 10 ቀን የምእመናኑ አብዛኛው ሥራ ውኃውን መከተር እና መገደብ በመሆኑ ዕለቱ ከተራ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል።
የጥምቀት ዋዜማ ታቦተ ሕጉ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ውኃ ባለበት አካባቢ ስለሚያድር የየአጥቢያው ሕዝብ እየተሰበሰበ በወንዝ ዳር ወይም በምንጭ አካባቢ ድንኳን ይተከላል።
ድንኳንም ከሌለ ዳስ ሲጥል ይውላል። የምንጮች ውኃ ደካማ በመሆኑ እንዲጠራቀም ይከተራል። ጉድጓድ እየተቆፈረ ውኃው እንዳይሔድ ይገደባል። ውኃው የሚከተረው በማግስቱ ጥር 11 ቀን የጥምቀት በዓል ስለሚከበር ለሕዝቡ መጠመቂያ እንዲሆን ነው።
የባሕረ ጥምቀት (የታቦት ማደሪያ) ምንነት
በየሰበካው ቦታ ተለይቶ እና ተከልሎ ታቦታቱ በዳስ ወይም በድንኳን የሚያድሩበት፣ የተለያዩ የውኃ አካላት ተጠርገው የሚከተሩበት ወይም ሰው ሠራሽ የግድብ ውኃ የሚበጅበት ስፍራ “ባሕረ ጥምቀት” (“የታቦት ማደርያ”) እየተባለ ይጠራል።
የከተራ በዓል በኢትዮጵያ
ከዐፄ ገብረ መስቀል ጀምሮ የአደባባይ በዓል የሆነው የጥምቀት በዓል በ15ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያዊው ንጉሠ ነገሥት ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ (1426-1460 ዓ.ም) አማካኝነት ታቦታቱ ወደ ወንዝ ወርደው ዕለቱን እንዳይመለሱ፣ በዚያ ፈንታ በጥምቀት ዋዜማ ጥር 10 ቀን ከሰዓት በኋላ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ ወርደው እንዲያድሩ ዐዋጅ ወሰኑ።
ይህን ታሪክ በመከተል ዐፄ ናዖድ (1486-1500 ዓ.ም) ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ምእመን ታቦተ ሕጉ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ በሚወርድበት እና ከባሕረ ጥምቀቱ ወደ ቤተ መቅደሱ በሚመለስበት ጊዜ አጅቦ አውርዶ፣ አጅቦ መመለስ እንዳለበት በዐዋጅ አስነግረው ነበር። ሕዝቡም ታቦታተ ሕጉን በሆታ እና በእልልታ ከቤተ መቅደስ አጅቦ ካወጣ በኋላ በባሕረ ጥምቀት ከትሞ ማደር ጀመረ።
የከተራ ዕለት ጥር 10 ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የሔደበትን የሚዘክር በዓል ነው።
በዕለቱ ድንኳን ተተክሎ፣ ዳሱ ተጥሎ እና ውኃው ተከትሮ ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ታቦተ ሕጉ የሚንቀሳቀስበት ሰዓት ሲደርስ የየቤተ መቅደሱ ታቦታት በወርቅ እና በብር መጎናጸፊያ እየተሸፈኑ በተለያየ ኅብር በተሸለሙ የክህነት አልባሳት በደመቁ ካህናት ከቤተ መቅደስ ወደ አብሕርት /ምጥማቃት/ ለመሔድ ሲነሡ መላው አብያተ ክርስቲያናት የደወል ድምፅ ያሰማሉ።
ምእመናን ከልጅ እስከ ዐዋቂ በዐጸደ ቤተ ክርስቲያን እና ታቦታቱ በሚያልፉባቸው መንገዶች “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ …’’ እንደሚባለው ያማረ ልብሳቸውን ለብሰው በዓሉን ያደምቃሉ። ጉዞም በዝግታ ወደ ጥምቀተ ባሕር ይሆናል።
ታቦታቱ በጥምቀት ዋዜማ ከመንበራቸው ወደ ጥምቀተ ባሕር መውረዳቸው እና በዚያ ማደራቸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ከማታው ጀምሮ መውረዱን እና ተሰልፎ ተራውን ሲጠብቅ ማደሩን ያመለክታል።
በመሆኑም ከዮሐንስ ለመጠመቅ የሚሄዱ ሰዎች ሁሉ በዮርዳኖስ ዙሪያ ድንኳናቸውን ተክለው ያርፉ ነበር።
ከዚህ አንጻር ዛሬም በባሕረ ጥምቀት ዙሪያ ድንኳኖች ዳሶች ይጣላሉ። የከተራ በዓል ታሪካዊ፣ ሃይማኖታ እና ትውፊታዊ ትርጉሙም ይህ ሲሆን ኦርቶዶክሳውያንም ታቦት ይዘው፣ ከወንዝ ወርደው፣ ድንኳን ተክለው የማክበራቸው መነሻውም መሆኑን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።