ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሙስናን የሚፀየፍ ሀገር ተረካቢ የማፍራት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን አሳሰበ።
ኮሚሽኑ “መልካም ስነምግባር ያሸልማል” በሚል መሪ ሀሳብ የትምህርት ተቋማትና ተማሪዎች እውቅናና ሽልማት መርሃግብር አካሂዷል።
በመርሐ-ግብሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀማል ረዲ የትውልድ ግንባታ መሰረት ከሆነው ከትምህርት ቤት ጀምሮ ሙስናን የሚፀየፍ ሀገር ተረካቢ የማፍራት ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው አሳስበዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ከ1 ሺ 56 በላይ ትምህርት ቤቶች መካከል ዓመቱን ሙሉ ሲካሄድ የቆየው የግንዛቤ ማስጨበጫና የውድድር ዝግጅቶችም መልካም የልምድ ልውውጥና ግንዛቤ ፈጠራ የተሰራባቸው መሆናቸውንም ገልፀዋል።
የትውልድ ስነ-ምግባር ማነፅ፣ የስነ-ምግባር እሴቶች ማጎልበትና የሞራል እሴቶች መገንባት ሙስናን የሚፀየፍ ትውልድ ለመፍጠር ወሳኝ መሆናቸውንም ኮሚሽነር ጀማል አስገንዝበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ትምህርት ቤቶች እውቀትና ክህሎትን ከማስጨበጥ ባሻገር የስነ-ምግባር እሴቶችን የተላበሰ ዜጋ የማፍራት ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው ብለዋል።
በይታያል አጥናፉ