ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለቀጣይ 90 ቀናት በሚከናወነው ልዩ የንቅናቄ አጀንዳ ዙሪያ ለመላው አመራር የስራ አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡
ይህ የልዩ ተልዕኮ አጀንዳ ከሰኔ 5 እስከ ጳጉሜ 5 ባሉ 90 ቀናት የሚከናወን ስሆን 18 ዋና ዋና ተግባራትን አካትቶ ይዟል። ከነዚህ የንቅናቄ አጀንዳዎች መካከል የከተማ ግብርናን ማስፋፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ መርሃግብርን ማሳካት ፣ የክረምት በጎ ፍቃድ ስራዎች፣ የኑሮ ውድነትን መቆጣጠር፣ ሁለተኛ ዙር ኮሪደር ልማትን ማጠናቀቅ፣ የትምህርት ለትውልድ ኢኒሼቲቭ፣ ገቢን ማሳደግ፣ እየተገነቡ የሚገኙ ትላልቅ ፕሮጄክቶችን (Mega Projects) አጠናቅቆ ለህዝብ ክፍት ማድረግ፣ ስራ ዕድል ፈጠራ እና ፍትሃዊ አገልግሎትን ለህዝባችን ተደራሽ ማድረግ አንኳሮቹ ናቸው።
እነዚህንና ተያያዥ የለውጥ የንቅናቄ ተግባራትን ለማሳካት አመራሩ በተቀናጀና በተናበበ መልኩ በመንቀሳቀስ የህዝባችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ይገባዋል ያሉት ከንቲባዋ የዚህ ልዩ ተልዕኮ ዋነኛው ፈጻሚ ሀይል ደግሞ ከከተማ ማዕከል ጀምሮ እስከ ወረዳ ያሉ ተቋሞችና የአስተዳደር ካላት ይሆናሉ ብለዋል።

በመሆኑም ሁሉም ተቋማት ምን ያህል “ሰራተኛን የልማት አቅም ማድረግ ችለናል?” የሚለዉ ዋነኛ መመዘኛችን ይሆናል ያሉት ከንቲባ አዳነች ትልቁ የልማታችን ሞተር የሆነው የህዝባችንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥብቅ የድጋፍና ክትትል ስርዓት በመዘርጋት እያንዳንዱን የንቅናቄ አጀንዳ ስኬታማነት ኦዲት እያደረግን እንሄዳለን ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሀላፊ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው የአዲስ አበባ አመራር ግዙፍ የሆኑ የልማት ስራዎችን በጥራት እና በአጠረ ጊዜ የማሳካት ቅንጅታዊ ብቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን በማንሳት ይህ የክረምት ንቅናቄ አጀንዳም የፓርቲ እና የመንግሥት አቅሞችን በማስተባበር ማሳካት ይቻላልማለታቸዉን ከከንቲባ ጽ/ቤት ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡