AMN – ታኅሣሥ 28/2017 ዓ.ም
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተሞች ከባለሃብቶች ጋር በመተባበር የገነባናቸው ቤቶች እና የስራ እድል ለተፈጠረላቸው የልማት ተነሺ የከተማችን ነዋሪዎች የመስሪያ ቦታዎችን አስተላልፈን እንኳን አደረሳችሁ ብለን ማዕድ አጋርተናል ብለዋል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ብቻ በኮሪደር ልማትና በመንገድ ወሰን ማስከበር ለተነሱ 4ሺ 510 እማወራ እና አባወራዎች ንጹህ እና መሠረተ ልማት የተሟሉላቸው መኖሪያ ቤቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብተን ያስተላለፍን ሲሆን 1264 በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች ደግሞ የስራ እድል ፈጥረን የመስሪያ ቦታዎችን አስረክበናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
አዳዲስ 4 ህንጻዎች በአያት ሪል ስቴት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ጄ ኤፍ ኤም ፔትሮሊየም ዲስትሪቢዩሽን እንዲሁም በለሚኩራ ክፍለ ከተማ የተገነቡ ሲሆን በተጨማሪም በላይነህ ክንዴ ግሩፕ በአቃቂ ቃሊቲ 48 ቤቶችን እንዲሁም በንፋስ ስልክ ላፍቶ 141 ቤቶችን ገንብተን ለነዋሪዎች አስተላልፈናልም ብለዋል ፡፡
መንግስት ያቀረበውን ጥሪ በመቀበል ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን የተወጡ ባለሃብቶችን በነዋሪዎቹ እና በከተማ አስተዳደራችን ስም ላመሰግናቸው እወዳለሁ ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡