የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከለውጡ ወዲህ የበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት የአንድ ወቅት የንቅናቄ ስራ ብቻ ሳይሆን የሁል ጊዜ ተግባር እና ባህል ማድረግን ታሳቢ በማድረግ ተቋም መስርተን፣ ተቋማዊ አሰራርን በመዘርጋት ባከናወንነው ስራ የሚሊዮኖች እንባ ታብሷል ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
ከንቲባዋ በዛሬው ዕለት ያስጀመርነው የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትም የበርካቶች እምባ የሚታበስበት፣ ለአቅመ ደካሞች 2,500 ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶች በመገንባት የዘመሙ ጎጆዎች የሚቃኑበት፣ ለ500,000 ሰዎች ማዕድ በማጋራት የክረምት የኑሮ ጫናን ማለፍ የምናስችልበት፣ ወላጅ የሌላቸዉ 440 ህፃናት አሳዳጊና ተንከባካቢ ቤተሰቦች የሚያገኙበት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በመትከል ከተማችንን አረንጓዴ የምናለብስበት እና ሌሎች በርካታ ስራዎችን የምንሰራበት አያሌ ዝርዝር ተግባራትን ያቀፈ ነው ሲሉ አብራርተዋል፡፡
በምሳሌነት የምንገልጻችሁ የከተማችን ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና ተቋማት በሙሉ በተለመደው መልኩ በገንዘባችሁ፣ በጉልበታችሁ እና በእውቀታችሁ እስካሁን ላበረከታችሁት ታሪካዊ አስተዋጽኦ አመሰግናለሁ ያሉት ከንቲባ አዳነች በቀጣይም አብራችሁን እንድትሰሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡