
AMN ግንቦት 13/2017 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ በአንድ ጊዜ 1ሺህ መኪኖችን የማቆም አቅም ያለውን እና በሾላ ገበያና መገናኛ መካከል ያለውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ የሚያቃልለውን የየካ ቁጥር 2 የመኪና ማቆሚያን መርቀው አገልግሎት ማስጀመራቸውን ገልጸዋል::
ከንቲባዋ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ይህ የመኪና ማቆሚያ ከምድር በላይ ባለ አምስት ወለል እንዲሁም በመሬት ውስጥ ባለ ሁለት ወለል በጥቅሉ 8 ወለል ያለው ምቹ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት እንዲሁም የህዝብን እንግልት የሚያቃልል መሆኑንም ጠቁመዋል::

የመኪና ማቆሚያው የህዝባችን አገልግሎት ምቾትና ክብርን የጠበቀ፣ ተገልጋዮችን ከዝናብና ፀሃይ የገላገለ፣ የንፅህና መጠበቂያ ያለው፣ የሰው እና የመኪና አሳንሰር ያለው፣ ለአካል ጉዳተኞች አካታች የሆነ አገልግሎት የሚሰጥ፣ ሶስት የመኪና ማጠቢያ ስፍራ ያለው እንዲሁም ለነዋሪዎች የስራ እድል የሚፈጥር ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነም አመላክተዋል።
በተጨማሪም ሌሎች አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሱቆች እና ቢሮዎች ያሉት የኢኮኖሚና የማህበራዊ አገልግሎትን ለማሳለጥ እንዲሁም የትራንስፖርት ስርአቱን ለማዘመን ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው እንደሆነም ገልጸዋል።

የተሽከርካሪ ማቆሚያው ለመጀመሪያ ጊዜ በህንጻ ደረጃ የተገነባ ሲሆን፣ መሬት እና በጀት በመመደብ የተሰራው ይህ ስራ ከተማችንን እንደ ስሟ ውብ አበባ የማድረግ አካል ነው ብለዋል::
ከለውጡ በፊት በመንግስት የተገነቡ የፓርኪንግ ቦታዎች ብዛት 2 ሲሆን 500 በላይ መኪኖችን የማቆም አቅም ያልነበራቸው እንዲሁ 1 ተርሚናል ብቻ የነበረዉን ከለውጡ በኃላ በሰራነው ስራ 150 የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን የገነባን ሲሆን የዛሬውን ጨምሮ 35 ሺሕ ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ማቆም የሚችሉ እንዲሁም 49 የሚደርሱ ተርሚናሎችን ገንብተን የትራንስፖርት ስርዓቱን ለማዘመን በመስራት ላይ እንገኛለን ሲሉም አክለዋል::
