የአዲስ አበባ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባስተላለፉት መልእክት ዛሬ 5 ኛዉን ግዙፍ እና ዘመናዊ የገበያ ማእከል አጠናቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ብለዋል፡፡
ለህዝባችን ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች የምንሰጣቸው ምላሾች ተጨባጭና መሰረታዊ ለዉጥ የሚያመጡ ናቸው፡፡
የኢፌዴሪ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ጋር በመሆን አምራቹንና ሸማቹ ህዝባችንን እንደ ድልድይ ሆኖ በቀጥታ በማገነኘት የኑሮ ውድነቱን እና የዋጋ ንረትን በመቀነስ የነዋሪዎቻችንን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚያስችል የላፍቶ ቁጥር 2 የገበያ ማዕከልን መርቀን ለአገልግሎት ክፍት አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
እስካሁን ካከናወናቸው በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ካላቸው ፕሮጀክቶች መካከል የኑሮ ውድነት እና የዋጋ ንረትን በመቀነስ ረገድ ጉልህ አስተዋጽዎ እያበረከቱ የሚገኙ በከተማችን አምስቱም በሮች ማለትም በላፍቶ፣ አቃቂ ቃሊቲ፣ ለሚ ኩራ እና ኮልፌ ክፍለ ከተሞች ዉስጥ ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙት የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡
እነዚህ የገበያ ማዕከላትን በመገንባት የአሰራር ስርዓት ዘርግተን ስራ ዉስጥ ማስገባት በመቻላችን በርካታ ዉጤቶች የተመዘገቡ ሲሆን፣ በተለይም ከዚህ ቀደም በአምራች እና በሸማቹ ህዝባችን መካከል ጋሬጣ ሆኖ የነበረዉ የደላላ ሰንሰለትን መቆራረጥ በመቻላችን በዉድድር ላይ የተመሰረተ የግብይት ስርዓት በመፈጠሩ ህዝባችን እፎይታን አግኝቷል።
ዛሬ የተከፈቱትን 159 ሱቆች ጨምሮ እስካሁን በተገነቡት ማዕከላት ዉስጥ 1037 ሱቆችና ግዙፍ መጋዘኖች አገልግሎት በመስጠት ላይ ያሉ ስሆን፤ በዛሬዉ ዕለት መርቀን ለአገልግሎት ክፍት ያደረግነዉ የላፍቶ ቁጥር 2 የምርት ግብይት ማዕከልም 8.8 ሄክታር ላይ የተገነባ፣ 159 ሰፋፊና ምቹ ሱቆችን፣ 9 የጅምላ ማከፋፊያዎች እና 2 ሞሎችን የያዘ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ለጀመርነው ሁለንተናዊ ለውጥ ትልቅ አቅምን የሚፈጥር ነዉ።
እነዚህ የገበያ ማዕከላት አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ወዲህ ከዚህ ቀደም የምርት መደበቅ ሴራ እና ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማስወገድ ለህዝባችን አለኝታ መሆን ስለቻላችሁ በነዋሪው ህዝባችንና በከተማ አስተዳደራችን ስም ያለንን አድናቆት እየገለጽን፣ ለገበያ ማዕከሉ ግንባታ ቦታቸውን የለቀቁ በግብርና ስራ የሚተዳደሩ የከተማችን ነዋሪዎች፣ ለዲዛይንን እና ግንባታ በሮ፣ ለኮንትራክተሩ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ድርጅት እና ለአማካሪው ኢንጂነሪንግ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልእክታቸዉ፡፡