ከኢትዮጵያኒዝም እስከ ፓን አፍሪካኒዝም

You are currently viewing ከኢትዮጵያኒዝም እስከ ፓን አፍሪካኒዝም

ቅኝ ገዥ አውሮፓውያን እ.ኤ.አ በ1884 በበርሊን ከተማ አፍሪካን ለመቀራመት ተስማሙ፡፡ ስምምነቱን ገቢራዊ ሲያደርጉት አፍሪካን እስኪበቃቸው ድረስ በዘበዙ፡፡ የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች ያለማንም ከልካይ ተዘረፉ። የአፍሪካዊያን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቻው ተረገጡ፡፡

በአፍሪካዊያኑ ላይ የሚደርሰው ጭቆና ታዲያ ጥቁር አፍሪካዊያንን ወደ አንድነት የሚያመጣ የትግል ምዕራፍ ከፈተላቸው፡፡

በተለይም ደግሞ እ.ኤ.አ በ1896 ዓ.ም ኢትዮጵያ ጣሊያንን በዓድዋ ድል መንሳቷን ተከትሎ ‘ኢትዮጵያኒዝም’ የተሰኘ ንቅናቄ በስፋት ተቀነቀነ፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያኒዝም የሚለው የነጻነት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከዓድዋ ድል ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ1880ዎቹ ሲሆን ከሰሃራ በታች ባሉ አፍሪካውያን የተደረገ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ መሆኑ ይገለፃል፡፡ የንቅናቄው ዓላማ ከቅኝ ገዥዎች ጭቆና ነፃ የወጡ የአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናትን ለማደራጀት ዓላማ ያደረገ ነበር፡፡

ከኢትዮጵያኒዝም እንቅስቃሴ ቀጥሎ አፍሪካዊያን ለነፃነታቸው በታገሉባቸው ዓመታት ውስጥ አንድነታቸውን ለማጠናከር ትልቅ ውጤት ማምጣቱ የሚነገርልት የፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ተቀጣጠለ፡፡

ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካዊያን እንዲሁም ከአፍሪካ የተሰደዱ ሁሉ ተመሳሳይ ፍላጎት ስላላቸው አንድ ሊሆኑ ይገባል የሚል እሳቤን የያዘ ነው፡፡

እንቅስቃሴው ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን፣ ኩዋሜ ንክሩማህን፣ ሙአመር ጋዳፊን፣ ቶማስ ሳንካራን እና ሌሎች ታላላቅ አፍሪካዊያን መሪዎችን ያፈራ ነው፡፡

የፓን አፍሪካኒዝምን ጽንሰ ሀሳብ የፈጠሩት በአሜሪካ እና በካሪቢያን ይኖሩ የነበሩ ጥቁሮች ቢሆንም የንቅናቄው ብርታት ኢትዮጵያ እንደነበረች ታሪክ ያስረዳል። ለነጮች ያልተንበረከከችና ነፃነቷን ጠብቃ የኖረች ብቸኛ ሀገር ኢትዮጵያ መሆኗን ከማመንም በላይ የኢትዮጵያ ነፃነት የአፍሪካ እና የጥቁር ህዝቦች ሁሉ ተደርጎ እንዲቆጠር ሆኗል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እና ፓን አፍሪካኒዝም  

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እኤአ ግንቦት 25 ቀን 1963 ነበረወ በአዲስ አበባ የተመሰረተው። የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከመመስረቱ በፊት በነበሩ ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ከድርጅቱ መመሥረት ጋር ተያይዞ በአፍሪካዊያን መካከል ክፍፍል ተፈጥሮ ነበር፡፡ ክፍፍሉም ካዛብላንካ እና ሞኖሮቪያ ይሰኛል፡

የካዛብላንካው ጎራ የአፍሪካ አንድነት ከመቋቋሙ በፊት ሀገራት ተዋህደው አንድ ሊሆኑ ይገባል የሚል ሲሆን የሞኖሮቭያው ደግሞ መተባባር ይቀድማል የሚል ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ክፍፍሉን ለማስታረቅ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ሥራ ከውናለች፡፡

የዲፕሎማሲ ብልሀቷና ብቃቷ የተከፋፈለውን ጎራ አንድ በማድረግ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመሥረት  አስቻይ ሁኔታን ፈጥሯል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለማቋቋም በተደረገው ከፍተኛ ተጋድሎ ውስጥ የኢትዮጵያ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ሁሌም በአፍሪካዊያን ስትታወስ ትኖራለች፡፡

በወቅቱም 30 ነፃ የወጡ አፍሪካ ሀገራትን በማስተባበር የመሪነት ሚናን ተጫውታለች፡፡

የአፍሪከ አንድነት ድርጅተ ሲመሠረት ከ20 በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት አልተላቀቁም ነበር፡፡ ድርጅቱ ከአፍሪካ ውጭ የነበረው የጥቁሮች የነፃነት እንቅስቃሴ በአንድነት ወደ አፍሪካ አህጉር እንዲመጣ አስችሏል፡፡

ታዲያ የድርጅቱ የመጀመሪያ አላማው በቅኝ ግዛት ሥር ያሉ ሀገራትን ነፃ ማውጣት ነበር ፡፡ ይህን በማሳካት ሥራን አሀዱ ብሎ የጀመረው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በበርካታ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ ስያሜውንም ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ህብረት ለመቀየር ችሏል፡፡

ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት ድርጅቱ የተቋቋመለትን ዓላማ  ማሳካት እየተሳነው በመምጣቱ ነው፡፡ ድርጅቱ በአህጉሪቱ ሠላምና ልማት ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ይልቁን ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭቶች መበራከት የድርጅቱን የማስፈጸም አቅም አዳክሟል፡፡የአፍሪካ መሪዎችም ድርጅቱን ከመደገፍ ይልቅ በድርጅቱ ላይ ለዘብተኛ መሆን ጀመሩ፡፡አባላቱ በሚጠበቀው ልክ የገንዘብ መዋጮ ባልማድረጋቸውም ድርጅቱ ተዳከመ፡፡

ይህን የተገነዘቡ የአፍሪካ ሀገራት የቀደመውን ችግር የሚቀርፍ እና ለአፍሪካ ማህበራዊ ፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊ መፍትሔ ሊያመጣ የሚችል አንድ አዲስ ተቋም ለመመሥረት አቀዱ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ወደ ‘አፍሪካ ህብረት’ በሚል ለመቀየር ያስቻለው ምክንያትም ይሄው ነው፡፡

በመሆኑም የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ሕብረት የተለወጠው በፈረንጆቹ 1995 ነው፡፡53 አባል ሀገራትን በመያዝም በአዲስ መልክ በጉዳዮች ላይ የመወሰን አቅሙን አሳድጎ ወደ አፍሪካ ሕብረት ተቀየረ፡፡

የሕብረቱ ፕሬዝዳንት  ሆነው የተመረጡትም የያኔው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት የነበሩት ታቦ ምቤኪ ናቸው፡፡

የአፍሪካ ሕብረት ተብሎ ከተመሠረተ በኋላ ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶቹን ለመሙላት  ብዙ ታትሯል፡፡ ግጭቶችን ማስቀረት፣ ሠላምን ማስፈን፣ ሥልጣን በመፈንቅለ መንግስት መያዝን በማውገዝ፣ ልማትን በማምጣትና ለዴሞክራሲ ሥርዓትም የተቻለውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

ከተመሠረተ 62 ዓመት የሞላው የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ የአፍሪካ ሀገራትን ነፃ ማውጣቱ፣ ሰላምና ደህንነትን ማስፈኑ፣ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ማምጣቱ፣ አለም አቀፍ ተሰሚነት፣ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የአፍሪካ ሕብረት ስኬት ተደርገው የሚነሱ መልካም ሥራዎች ናቸው፡፡

በአንፃሩ ለውጭ ርዕዮተ አለም ተጋላጭነት፣ግጭቶችን ሙሉ በሙሉ ማስቆም አለመቻል፣ ከአባል ሀገራት የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍ ማነስ የማስፈፀም አቅም ላይ ውስንነት መፍጠሩ እንዲሁም ሙስና የህብረቱ ድክመቶች ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡

የአፍሪካ ሕብረት የማስፈፀም አቅሙን ማሳደግ፣ በወጣቶች የተሞላች አህጉር እንደመሆኗ ሥራ እድል ፈጠራ ላይ መሥራት፣ ውስጣዊ የገቢ አቅምን ማሳደግ እና የሕዝብ ተሳትፎን ማጠናከር ቀጣይ የቤት ሥራዎች ሆነው ይቀጥላሉ፡፡

በአዲስ አበባ በሚካሄደው 38ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የአባል ሀገራቱ መሪዎች አዲስ አበባ እየገቡ ነው፡፡

ሱዳን በ2021 በምርጫ ወደ ሥልጣን በመጡት ፕሬዝዳንተ አብዱላህ ሀምዶክ ላይ ባካሄደችው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ምክንያት ከሕብረቱ በጊዜያዊነት ታግዳለች፡፡

ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊና ጊኒም በኢ-ህገ መንግስታዊ አካሄድ የመንግስት ለውጥ ያደረጉ በመሆኑ ሕብረቱ ከጉባኤው ያገዳቸው መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡

በማሬ ቃጦ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review