ከከተማ ወደ ገጠር የፈነጠቀው ብርሃን

You are currently viewing  ከከተማ ወደ ገጠር የፈነጠቀው ብርሃን

“እምዬ ኢትዮጵያ” በሚለው የቴዎድሮስ ታደሰ ዘመን ተሻጋሪ የዘፈን ግጥም ውስጥ እልፍ ቁምነገሮች አሉ፡፡

“እምዬ ኢትዮጵያ ይመርልሽ ሰብሉ

አውድማው ጎተራዉ ይሁንልሽ ሙሉ

በቸር ዉሎ ይደር ጋራ ሸንተረርሽ ወንዛ ወንዝሽ ሁሉ፡፡” ይላታል ድምፃዊው፤ አዎ!  ሀገራችን ከራስ ፀጉሯ እስከ እግር ጥፍሯ ድረስ ሰላም ትሁን፡፡ ግን ደግሞ የጎተራው ባለቤት፣ የልማቱ ጌታ፣ የገጠሩ ነዋሪ ያ! የሁላችን ምንጭ፣ አርሶና አርብቶ አደሩ ኑሮው ለዘመናት ችላ የተባለ ነው፡፡ ከእንስሳቱ ጋር አብሮ እያደረ  ከዓመት እስከ ዓመት ከተሜውን እየመገበ እርሱ ግን ሁሉ እያለው፣ ሁሉንም እየሰጠን ተጎሳቅሎ ውሎ፤ ተጎሳቅሎ  ያድራል፡፡

“በማጀትሽ ወተት በጤፍሽ እንጀራ

በማር በወለላሽ በጓሮሽ ሸንኮራ”  እንዳለው፣ የገጠሩ ነዋሪ ሁሉ በጁ ሁሉ በደጁ ነው፡፡ እንግዳ  ሲቀበል፣ ሲደግስ፣ ሲለግስ ስስትን አያውቅም፡፡ ዋናው ቁምነገር “ብድር አለብኝ ልክፈልና ልኩራ” እሚለው ስንኝ ላይ ነው፡፡ ያ! ያበቀለንን ምድር፣ ያሳደገንን የገጠሩ ነዋሪን ምን ያህል ብድሩን ከፍለነዋል?!

ያበቀለንን ቀዬ፣ ያበብንበትን ምድር፤ በአካልም ያሸትንበትን፣ ሜዳና መስኩን፣ ከዚህ አለፍ ሲልም ሳይማር ያስተማረንን የገጠሩን ወገናችንን ውለታ ምን ያህል መልሰናል? የሚለው ነጥብ  ሁሌም የማንቂያ ደውል ሆኖ በአርበ ልቦናችን እያቃጨለ ኖሯል፤ ይኖራል፡፡

“ለሁሉም ጊዜ አለው”  እንዲል መፅሐፉ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጭነትና የቅርብ ክትትል በአዲስ አበባ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ለሌሎች የሀገራችን ከተሞች ብቻ ሳይሆን ለገጠሩ ክፍልም የልማት ብርሃኑን እየፈነጠቀ ነው፡፡ በድምፃዊው ጠቆም የተደረገው “ብድር አለብኝ ልክፈልና ልኩራ” የሚለው ሀሳብ  በተግባር እየተገለጠ  ስለመሆኑ ምስክር አያሻም፡፡

ከሰሞኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ዱባንቾ ቀበሌ በገጠር ኮሪደር ሞዴል የአርሶ አደሮች መኖሪያ መንደር የማስጀመሪያ መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡  እነዚህ ማሳያ መንደሮች መገንባታቸው አርሶ አደሩ የግብርና ስራ እያከናወነ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ  ስለመሆናቸውም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገጠሩን ኑሮ  ሌላኛውን መጋረጃ በሚገባ ገልጠው የተጎሳቆለውን ኑሮ አስተውለን እንድናይ ከማድረጋቸው በፊት ፣

ወተቱ ከማጀት እሸቱ ከጓሮ፣

በጣም ያስደንቃል የገጠሩ ኑሮ…።”  እያልን በስንኝ ቋጠሮ  እንሸፋፍነው ነበር፡፡

እውቁ እንግሊዛዊ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሮበርት ጆን ሃይሎክ “Rural Development: Putting the Last First” ወይም ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት የተዘነጋውን አሊያም “የመጨረሻውን ማስቀደም” የተሰኘ ድንቅ መፅሐፍ አላቸው፡፡ በዚህ የምርምር ስራቸው እንደገለፁት የገጠር ድህነት፣ ኑሮና ሁኔታ ብዙውን ጊዜ በውጭ ሰዎች በወጉ የማይታይ ወይም የተዛባ ግምት የተሰጠው ነው። ይህም በመሆኑ የገጠር አካባቢዎች በቀላሉ ሊስተካከሉ በሚችሉ ችግሮች ወይም አስተሳሰቦች ምክንያት የድህነት መገለጫ ሆነዋል ይላሉ፡፡

እንደ ኢትዮጵያም ገጠሩን መሰረት ያደረጉ በርካታ ስራዎች በየዘመናቱ የተከናወኑ መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናት የሚያትቱ ቢሆኑም ገጠሩ ካለበት ችግር ወጥቶ ባለው ሀብትና ፀጋ ልክ የሚኖርበት ሁኔታ አለመፈጠሩ ግን ለብዙዎቻችን እንቆቅልሽና የሚያስቆጭም ነው፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተሟላ ብልፅግናን ማረጋገጥ እንዲቻል ሕይወትን በቤተሰብ ደረጃ መቀየር የሚያስችሉ ማዕቀፎችን ተግባራዊ ማድረግ ተጀምሯል፡፡ ለአብነት አረንጓዴ አሻራ፣  በምግብ እህል እራስን መቻል፣ የሌማት ትሩፋት፣ የኮሪደር ልማት እና መሰል የልማት መርሃ ግብሮች ወደ ተግባራዊ ምዕራፍ ተሸጋግረው ከቤተሰብ ተጠቃሚነት አለፍ ያለ ውጤትም እያስመዘገቡ ነው፡፡ የእነዚህ ስራዎች አላማም ሰብአዊ ልዕልናን ማረጋገጥ  እንደሆነ መንግስት ይፋ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)  የገጠር ኮሪደርን አስመልክቶ  ባስተላለፉት መልዕክታቸው፣ የገጠር ኮሪደር ማለት የእያንዳንዱን  አርሶ አደር ቤት  የአኗኗር ዘዬ መቀየር ማለት ነው፡፡ የዚህ መርሃ ግብር ዋናው አላማ በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን ሕይወት መቀየር ነው፡፡ ምክንያቱም የገጠሩ ነዋሪን የአኗኗር ዘዬው ካልተቀየረ በስተቀር በሀገር ደረጃ የምናስበውን ብልፅግና አናረጋግጥም፡፡ የለማ ሀገር መፍጠር የሚቻለው ከቤተሰብ የሚጀምር ሁለንተናዊ ልማትን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆነም መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡

ይህንን አስመልክቶ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ጀማ ሐጂ፣  በገጠሩ ክፍል በደንብ ገባ ብሎና ያላቸውን ሀብት ተረድቶ በቤተሰብ ደረጃ መስራት ለሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

ወደ ገጠሩ የማህበረሰብ ክፍል ቀረብ ብሎ ያላቸውን ሀብት፣ የትምህርት ደረጃ፣ የመሬት ስፋት፣ የቤተሰቡ አቅም እና መሰል ነገሮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህንን ሀብታቸውን ምን ላይ ቢያውሉ የተሻለ ምርታማ ይሆናሉ፣ ባላቸው ሀብት ልክስ እንዴት ሊኖሩ ይገባል፣ የሚለውን ማመቻቸትና መንግስትም ደከም በሚሉበት ቦታ ድጋፍ ከሰጠ  ምርታማነት ያድጋል፤ ይህ ማለት ደግሞ የሀገር ዕድገት በአስተማማኝ መልኩ እንዲረጋገጥ  ያግዛል ብለዋል፡፡

አክለውም ስልጠና በመስጠትም የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ ይህም የተሻለ ምርታማ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ከእርሻም ወጣ ያሉ ነገሮችንም እንዲሰሩ ማበረታታት ያስፈልጋል ያሉት ፕሮፌሰሩ በትክክል ከተሰራበትም የገጠር ኮሪደር ልማቱ ሀገርን ለመለወጥ የሚያስችል እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የስነ ልቦና አማካሪ አቶ ማህደር ሳላይህ እንደሚሉት እንደ ሀገር በቤተሰብ ላይ የሰራናቸው ተግባራት በብዙ መልኩ ክፍተት ያሉባቸው ናቸው፡፡ በተለይም  በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊም ሆነ በተለያዩ ዘርፎች ንቁ የሆኑ የቤተሰብ አባላትን በመፍጠር  ምቹና ጤናማ ሕይወትን የሚመራ፣  ለሀገር ዕድገት ባለው አቅምና ልክ የሚተጋ ትውልድን ከመፍጠር አንፃር የበለጠ መስራት ይኖርብናል። በሌላ በኩልም በዛ ያለው የገጠሩ የህብረተሰብ ክፍል የተመጣጠነ ምግብ፣ ልብስና መኖሪያ የማገኘት ዕድል እንኳ ቢኖረው ባለው ሀብት ልክ ያለመኖር ክፍተት ይታያል፡፡ ይህ ደግሞ ከግንዛቤ ክፍተት የሚመጣ ነው፡፡

በሌላ በኩልም ከመኖሪያ ቤቱ እራቅ ብሎ ያለውን እርሻውን እንጅ በጓሮው የተለያዩ ልማቶችን ማከናወን እንደሚችል በሚገባ የመረዳትና በዚያው ልክ የመስራትም ክፍተት ይስተዋላል። ስለሆነም  የገጠር ኮሪዶርን በመሳሰሉ ልማቶች በቤተሰብ ላይ በሁሉም ዘርፍ በመስራት ለለውጥ የሚተጋ ማህበረሰብን መፍጠር እንደሚያስፈልግም መክረዋል።

አክለውም በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውና በአስደናቂ ለውጥ የታጀበው የኮሪደር ልማት የሀገሪቱን ሌሎች ከተሞች ከማነቃቃት አልፎ ለገጠሩ ክፍልም ትልቅ ተምሳሌትና የልማት ስንቅ እየሆነ ነው፡፡  ይህም ከተማዋ በተለወጠች ቁጥር እንደሀገር ተምሳሌትነቷ ከፍ ይላል፡፡ ይህም በቀላሉ ሌሎች የሀገራችንን ክፍል ማልማት እንድንችል ስንቅና ጉልበት ይሆነናል፡፡ በአሁኑ ወቅትም በሀገሪቱ ከተሞች እና በገጠሩ ክፍል እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ስራዎች ለዚህ ማሳያ  እንደሆኑም አመላክተዋል፡፡

የገጠር አካባቢዎች እየዘመኑ እና እየበለጸጉ ሲሄዱ፣ የአኗኗር ዘይቤያቸው ይቀየራሉ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የተሻለ ሀብትን የሚያፈሩበት ዕድል ይፈጠራል፣ ነዋሪዎች በተሻለ የመኖሪያ ቤት እንዲኖሩ ያደርጋል፣ በትምህርት፣ በጤና እና መሰል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ውጤታማ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ያደርጋልም፡፡ ይህም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትን ከማረጋገጡም በላይ ሁለንተናዊ ደህንነቱ የተረጋገጠ ማህበረሰብንም ለመፍጠር እንደሚያግዝም ጠቁመዋል፡፡

በኮሪደር ልማት እንደ አዲስ አበባ፣ ውበቱ እንዲፈካ፣ አርሶና አርብቶ አደሩ ውሎና አዳሩ እንዲያምር፣ በአቅሙና በሚገባው ልክ  ደስ ብሎት እንዲኖር በምንችለው ሁሉ እንደግፈው ዘንድ ኑ! ገጠር እንሂድ፡፡

በመለሰ ተሰጋ    

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review