ከዚህ ቀደም በጨለማ የተዋጡ እና ወንጀል ሲፈፀምባቸው የነበሩ ስፍራዎችን በማህበረሰቡ እና የፀጥታ ሀይል ቅንጅት በብርሀን የተሞሉ እና አስተማማኝ ሰላም የሰፈነባቸው ማድረግ መቻሉን አዲስ አበባ ከተማ የሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ገለፁ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች እና ሌሎች የሚመለከታቸዉ አካላት በጉለሌ ክፍለ ከተማ የሰላም ሰራዊት የመስክ የስራ እንቅስቃሴ ምልከታ አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ፣ ለመዲናዋ የፀና እና የተረጋገጠ ሰላማዊ መሆን የፀጥታ ሀይሉ እና የህብረተሰቡ ቅንጅት ሚናው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

የሰላም ሰራዊት ከህዝብ የተገኘ ለህዝብም የሚሰራ የሰላም ዘብ ነው ያሉት ኃላፊዋ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ጨለማ የነበሩ ቦታዎችን ብርሀናማ በማድረግ እንዲሁም ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የሚሰራቸዉ ስራዎች የሚበረታቱ እና ልምድና ተሞክሮም የሚቀመርበት ነው ብለዋል፡፡
የጉለሌ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ወልዴ ወገሴ፤ በክፍለ ከተማው ጨለማን በብርሀን የመተካት አስተማማኝ ሰላምን ለማስቀጠልም ከህብረተሰብ ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
24 ሰዐት በማትተኛዋ አዲስ አበባ የፀና እና የተረጋገጠ ሰላምን ለማፅናት 24 ሰዐት ለመዲናዋ ዘብ እንደሚሆኑ ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታን ያደረጉ የሰላም ሰራዊት አባላት ገልፀዋል፡፡
በተመስገን ይመር