AMN-የካቲት 13/2017 ዓ.ም
ከፍተኛ የሆነ የደህንነት እና ጥራት ደረጃዎች አልፎ የተሠራ አዲስ ፓስፖርት በነገው ዕለት ይፋ እንደሚደረግ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት አስታወቀ፡፡
የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ጎሳ ደምሴ ለኤኤምኤን እንደተናገሩት፣ አገልግሎቱ በየብስ እና አየር ምቹ እና ነፃ የሰዎች ዝውውር እንዲኖር ቁጥጥር ማድርግ፣ የጉዞና የይለፍ ሰነዶችን መስጠት፣ የቪዛ አገልግሎት በሁሉም ቆንጽላዎች መስጠት፣የሲቪል እና ቤተሰብ ምዝገባ አገልግሎት እና ሌሎችንም በርካታ ኃላፊነቶች እየተወጣ ይገኛል፡፡
ይሁንና ተቋማዊ ቁመናው ኢትዮጵያን የሚመጥን ባለመሆኑ ለውጥ ማድረግ አስገዳጅ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ በተለይም ከ2010 ዓ.ም በፊት በዓመት ውስጥ 100ሺ ፓስፖርት እንኳን የማሰራጨት አቅም እንዳልነበረው በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ በአንፃሩ ከለውጡ ወዲህ እስከ 368 ሺ ፓስፖርት ድረስ በአንድ ዓመት መሠራጨቱን ገልጸዋል፡፡
በነገው ዕለት ይፋ የሚደረው አዲሱ ፓስፖርት ባዮግራፊክ መረጃ ብቻ ሳይሆን የግለሰቡን አሻራ የያዘ (ኤሌክትሮኒክስ ችፕስ) እንዳለውም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
ከፍተኛ የሆነ የደህንነት እና ጥራት ደረጃዎች አልፎ የተሠራው ይህ ፓስፖርት የደህንነት ቅንጣቱ ከቀድሞው ፓስፖርት በ300 እጅ ያደገ ነው ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው ፓስፖርት ዲዛይን በውጭ ሀገር የግል ተቋም እጅ የነበረ ሲሆን አዲሱ ፓስፖርት ግን ሙሉ በሙሉ ዲዛይኑ የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አዲሱ ፓስፖርት በሀገር ውስጥ ተመርቶ በዶላር ከመግዛት በዶላር ወደ መሸጥ የሚያሸጋግር መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
የቪዛ ቅጠሎቹ (ገጾች) ኢትዮጵያን የሚገልፁ ባህላዊ፣ ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና ሌሎች መገለጫዎች እንዲኖሩት መደረጉን በማንሳት ከሉሲ ጀምሮ እስከ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ድረስ በገጾቹ ውስጥ መካተታቸውን አብራርዋል፡፡
ተቋሙ ከፓስፖርት በተጨማሪ ለውጭ ዜጎች የሚሰጡ ቋሚ እና ጊዜያዊ የመኖሪያ ፈቃድ፣‘አሊያን’ የተሰኘ ለውጭ ዜጎች ብቻ የሚሰጡ መታወቂያ አገልግሎት ይሰጣል ተብሏል፡፡
ለውጭ ዜጎች የሚሰጠው አገልግሎት ቀደም ሲል የጥራት፣ የፎርጀሪ፣ ከዲጂታላይዜሽን እና ደህንነት አንጻር ክፍተት ነበረበት ብለዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከ33ሺ በላይ ሀሰተኛ ሰነድ አዘጋጅተው ሲገለገሉ የነበሩ የውጭ ዜጎች ተገኝተዋል ነው ያሉት አቶ ጎሳ፡፡
አዲስ የዲጂታላይዜሽን አሰራር ችግሩን የሚቀርፍ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ተመላክቷል፡፡
በማሬ ቃጦ