
AMN ግንቦት 12/2017 ዓ.ም
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር አይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔን በይፋ አስጀምረዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)ን ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ቴዎድሮስ ምህረት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የአይዲ ፎር አፍሪካ ሊቀ መንበር ጆሴፍ አቲክ(ዶ/ር)፣ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዮዳሄ ዘሚካኤል ተገኝተዋል፡፡
ከግንቦት 12 እስከ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም በሚቆየዉ ጉባዔ ላይ በአጠቃላይ 2 ሺህ 200 ታዳሚዎች የተሳተፉበት ሲሆን ከነዚህ መካከል 1ሺህ 800 ያህሉ ከ105 የዓለም ሃገራት የተውጣጡ ሲሆኑ 400 ያህሉ ደግሞ የሃገር ውስጥ ተሳታፊዎች ናቸዉ፡፡

ጉባዔውን ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ማንነት ከአሁን በኋላ አማራጭ ሳይሆን ሰዎችን ከአገልግሎቶች፣ ከማኅበረሰቦች፣ ከተቋማት እና ከመንግሥታት ጋር የሚያገናኝ አስፈላጊ መሠረተ ልማት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
የአይዲ ፎር አፍሪካ ሊቀመንበር ጆሴፍ አቲክ በበኩላቸው በአፍሪካ ዲጂታል ማንነት ላይ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአፍሪካን ሁለንተናዊ ልማትና የዜጎች ኑሮ ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።

ጉባኤው በአዲስ አበባ መካሄዱ መዲናዋን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተያዘዉን ራዕይ የሚያጠናክር መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በሊያት ካሳሁን