
AMN – ግንቦት 6/2017 ዓ.ም
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ወደ ኳታር ከማቅናታቸው በፊት በሳዑዲ አረቢያ ከሶሪያው መሪ አህመድ አል-ሻራ ጋር መነጋገራቸውን ኋይት ሀውስ አስታውቋል።
ይህም እ.ኤ.አ ከ2000 በኋላ የአሜሪካ እና የሶሪያ መሪዎች የተገናኙበት መጀመሪያው እለት ያደርገዋል።
የሳውዲው አልጋ ወራሽ መሀመድ ቢን ሳልማን ስብሰባውን በመምራት የተሳተፉ ሲሆን፣ የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ደግሞ በስልክ ተቀላቅለዋል።
ሁለቱም መሪዎች፣ ትራምፕ በቀድሞ የሶሪያ ፕሬዝደንት በሽር አል-አሳድ የስልጣን ዘመን በሶሪያ ላይ ተጥሎ የነበረውን የረዥም ጊዜ ማዕቀብ ለማንሳት መወሰናቸውን አድንቀዋል።
በሀገራቸው ታሪካዊ ነገር ለመስራት ትልቅ እድል እንዳላቸው ለአል-ሻራ የተናገሩት ትራምፕ፣ የእስራኤልን ሉዓላዊነት እውቅና ለመስጠት የአረብ ሀገራት ማዕቀፍ በሆነው የአብርሃም ስምምነት ላይ እንዲፈርሙም አሳስበዋል።
አል-ሻራ እ.ኤ.አ. በ1974 ከእስራኤል ጋር ለተፈራረሙት ስምምነት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠው፣ የአሜሪካ ኩባንያዎች በሶሪያ ዘይትና ጋዝ ላይ ኢንቨስት እንዲያደርጉ መጋበዛቸውም ተዘግቧል ።
በሊያት ካሳሁን