ከ330 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

AMN – ታኅሣሥ 9 /2017 ዓ.ም

የጉምሩክ ኮሚሽን ከህዳር 27 እስከ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ባደረገው ክትትል 308.8 ሚሊዮን ብር የገቢ የኮንትሮባንድ እቃዎች እና 23.1 ሚሊዮን ብር የወጭ፤ በድምሩ 331.9 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡

በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ወርቅ፣ ቡና፣ ጥራጥሬ፣ የተሽከርካሪ መለዋወጫ፣ የመዋቢያ እቃዎች፣ ጫት፣ አደንዛዥ እጾች ፣ መድኃኒት፣ ምግብ ነክ እቃዎች ፣ የተለያዩ ተሽከርካሪዎች እና የውጭ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡

በተጠቀሰው የጊዜ ገደብ የገቢ እና የወጭ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ሀዋሳ፣ ሞያሌ እና ድሬድዋ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ በቅደም ተከተላቸውም 115 ሚሊዮን፣ 72 ሚሊዮን እና 49 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል፡፡

የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ ፣ በበረራ እና በደፈጣ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 30 ተጠርጣሪ ግለሰቦች እና 12 ተሽከርካሪዎችም በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች እና አመራሮች፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን ያደርሳል፡፡

የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ማቅረቡ ከኮሚሽኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review