ከ580 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ላይ ናቸው

You are currently viewing ከ580 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ላይ ናቸው

AMN – መጋቢት 16/2017

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ580 ሺህ በላይ ዜጎች የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ላይ መሆናቸውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታወቀ::

ስልጠናውን ያጠናቀቁ ከ180 ሺህ በላይ የሚሆኑት ዜጎች የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

መርኃ ግብሩ በኢትዮጵያ መንግስትና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እገዛ የሚተገበር የዲጂታል ሥራ ክህሎት ማሳደጊያ የትብብር ፕሮጀክት ነው።

ፕሮጀክቱ “ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር” በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት አምስት ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ ዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።

በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የአይሲቲና ዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ይሹሩን አለማየሁ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ መርኃ ግብሩ የዲጂታል ክህሎትን መገንባት ያስችላል።

በመርኃ ግብሩ ከ580 ሺህ በላይ ዜጎች ተመዝግበው ስልጠናውን እየተከታተሉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል180 ሺህ የሚሆኑት ስልጠናውን በማጠናቀቅ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረር የአምስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ ስልጠና አፈፃፀም የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

መርኃ ግብሩን የተሳካ ለማድረግ ሌሎች ክልሎች በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበው ሚኒስቴሩም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

ስልጠናው የፈጠራ ስራን ለማበረታታት የሚያግዝ በመሆኑ በተለይ ወጣቶች ይህን እድል ተጠቅመው ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው ማስረዳታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review