በመዲናችን አዲስ አበባ ባለፉት ቀናት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም በመዲናችን የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች የተሰናዱ ሲሆን፣ ከእነዚህ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የስዕል አውደ ርዕይ፣ የአዳዲስ መጽሐፍ ህትመት፣ የሙዚቃ ዝግጅት፣ የቴአትር መርሃ ግብር፣ እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል መርሃ ግብሮቹን እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
ሙዚቃ
የዓለም የሥነ ጥበብ ቀን እና የኢትዮጵያ ጃዝ ፌስቲቫል ይካሄዳል፡፡ ዛሬ ቅዳሜና እሁድ፤ ማለትም ሚያዝያ 25 እና 26 ቀን 2017 ዓ.ም ዓለም አቀፍ የጃዝ ሙዚቃ ዝግጅት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ማዕከል ውስጥ ይደረጋል፡፡ የዘንድሮው ፌስቲቫል ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ሀገራት ታዋቂና እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ሙዚቀኞችን ያሳተፈ መሆኑን ታውቋል፡፡ የፌስቲቫሉ አዘጋጆች የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚና ሴይ ሪከርድ ናቸው።
በፌስቲቫሉ ከሚሳተፉት ታዋቂ ከያኒያን መካከል ሙዚቀኛ አበጋዝ ክብረወርቅ ከዝነኛው አድማስ ባንድ ጋር፣ ነጋሪት ባንድ፣ ታዋቂው የፒያኖ ተጫዋችና አቀናባሪ ሳሙኤል ይርጋ ከባንድ ቡድኑ ጋር፣ ጆርጋ መስፍን ከአስሊ ኢትዮ ጃዝ ባንድ ጋር፣ መሃሪ ብራዘርስ ባንድ፣ ሔዋን መሸሻ ከሙሉ ባንዷ ጋር፣ የአፍሪካ ሙዚቃ አቀንቃኟ ናንሲ ሙቲዚ ከዚምባቡዌና ሌሎችም ተጋባዥ ከያኒያን በመድረኩ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
ለሁለት ቀናት በሚቆየው ይህ ፌስቲቫል፣ በርካታ የኪነ ጥበብ አፍቃሪያን ከሀገር ውስጥና ከውጭ ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የዚህ ዓመት ፌስቲቫል ለኢትዮ-ጃዝ አባት ሙላቱ አስታጥቄ በዘርፉ ላበረከተው ፈር ቀዳጅ ሥራዎቹ እና በዓለም የሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ላኖረው ሙዚቃዊ ትሩፋት ክብር የተሰጠ እንደሆነም ታውቋል። በተጨማሪም በቅርቡ በሞት የተለየው ዕውቁን የድራም ተጫዋችና አቀናባሪ ተፈሪ አሰፋን ይታሰብበታል ተብሏል፡፡

ዝግጅቱ ዛሬ ቅዳሜና ነገ እሁድ የሚካሄድ ሲሆን፣ ፕሮግራሙ የሚጀምረው ደግሞ ከሰዓት 7፡00 ሰዓት እስከ ምሽት 1፡00 ሰዓት ድረስ ነው ተብሏል፡፡ ዝግጅቱ የሚካሄደው ፓስተር አካባቢ የሚገኘው ጳውሎስ ሆስፒታል ጀርባ ባለው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ ነው፡፡
ሥዕል
በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የሥነ ጥበብ ሥራዎች ዓውደ-ርዕይ ዛሬ ይከፈታል፡፡ በአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት እና ከኢትዮጵያ ሰዓሊያን ማኅበር የተሰባሰቡ ምርጥ የሥነ ጥበብ ስብስቦች አውደ ርዕይ ዛሬ ቅዳሜ ከ7፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ውስጥ በሚገኘው የሥነ ጥበብ ማዕከል ውስጥ ለዕይታ ይቀርባሉ፡፡ የስዕል አውደ ርዕዩ ከዛሬ ከሚያዚያ 25 ቀን አንስቶ ለአስራ አምስት ቀናት ለተመልካች ክፍት ሆኖ ይቆያል ተብሏል፡፡ የሥዕል አውደ ርዕዩ በዕለቱ ከሚጀምረው የዓለም የሥነ- ጥበብ ቀን እና የኢትዮጵያ ጃዝ ፌስቲቫል ጎን ለጎን የሚካሄድ ነው ተብሏል፡፡ የሥነ ጥበብ አፍቃሪያንም አውደ ርዕዩ ላይ እንዲገኙና የሥነ ጥበብ ውጤቶችን እንዲመለከቱ ተጋብዘዋል፡፡
በሌላ መረጃ የአይዳ ሙሉነህ የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ በመታየት ላይ ነው፡፡ በአይዳ ሙሉነህ ተዘጋጅቶ በ ዘ-ኢንድ ፈንድ አዘጋጅነት እና በሪቺንግ ዘ-ላስት ማይል ድጋፍ ለህዝብ የቀረበው ሪፍሬሚንግ ኔግሌክት የተሰኘ የፎቶ ዓውደ ርዕይ ባሳለፍነው ሳምንት በይፋ ተከፍቶ በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
በገብረክርስቶስ ደስታ ዘመናዊ የሥነ ጥበብ ማዕከል እየታየ ባለው በዚህ ዓውደ-ርዕይ፣ አይዳ ሙሉነህን ጨምሮ የሰባት አፍሪካዊ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ስራ ስብስብ ቀርቦ በመታየት ላይ እንደሆነም ኢቨንት አዲስ ሚዲያ ዘግቧል፡፡

በስራዎቻቸው ጠንካራ ታሪክን በፎቶ የማስቀረት እና ማህበረሰቡ የሚያልፍበትን እውነታ የማንፀባረቅ ድንቅ ችሎታ ያላቸው የስድስት አፍሪካዊ ባለሙያዎች 54 የስነ ጥበብ ስራዎችና ዘጋቢ-ፎቶዎች የተካተተበት ዓውደ-ርዕይ ስነ-ጥበብ ምን ያህል ወሳኝ ጉዳዮችን የማጉላት ትልቅ አቅም እንዳለው ያሳያሉ ተብሏል፡፡ ዓውደ-ርዕዩ ባለፈው ሚያዝያ 16 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ የተከፈተ ሲሆን እስከ ግንቦት 19 ቀን 2017ዓ.ም ለእይታ ክፍት ሆኖ ይቆያል፡፡
መጽሐፍት
በሥነ-አመክንዮና በጥልቅ አሰላሳይነት ዙሪያ የሚያጠነጥነው ‘An Introduction to Logic and Critical Thinking’ መጽሐፍ ለንባብ ሊበቃ ነው። መምህራን፣ ተማሪዎችና እንዲሁም ፍልስፍናን ማንበብ የሚወዱ መጻሕፍት አንባብያን በብዙ ረገድ የሚያግዝ መጽሐፍ ነው ተብሏል፡፡ መጽሐፉ የተጻፈው በፍልስፍና ምሁራኑ በፋሲል መራዊ(ዶ/ር) እና መምህር ቢኒያም መኮንን አማካይነት ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ አማካይነት የታተመው ይህ መጽሐፍ፣ በተለያዩ መጻሕፍት መደብር ይገኛል ተብሏል፡፡ በተያያዘ መረጃ መጽሐፉ የፊታችን ሐሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2017ዓ.ም ይመረቃል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ውስጥ በሚመረቀው በዚህ መጽሐፍ ምረቃ ላይ የተለያዩ ምሁራንና ተጋባዥ እንግዶች ይታደማሉ፡፡ የምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት እስከ 10፡30 ሰዓት ድረስ ይቆያል ፡፡
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ ከሚታዩ ቴአትሮች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ በብሔራዊ ቴአትር ቤት ባሎች እና ሚስቶች ቴአትር ቅዳሜ 8:00 ሰዓት፤ ባቡሩ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ 11፡30 ሰዓት ይታያል፡፡ እሁድ በብሔራዊ ቴአትር በ 8፡00 ሰዓት 12ቱ እንግዶች ቴአትር ለእይታ የሚቀርብ ሲሆን፤ እምዬ ብረቷ የተሰኘው ቴአትር ደግሞ 11፡30 ሰዓት ላይ ይታያል፡፡ እንዲሁም በቀጣይ ቀናት በቴአትር ቤቱ ማክሰኞ በ11፡30 ሰዓት ሦስቱ አይጦች፣ ረዕቡ በ11፡30 ሰዓት የቅርብ ሩቅ ቴአትር፣ ሐሙስ ቀን 11:30 ሰዓት ሸምጋይ ቴአትር፣ አርብ በ11፡30 ሰዓት የሕይወት ታሪክ ቴአትሮች ይታያሉ፡፡ በዓለም ሲኒማ ለጥበብ አፍቃሪያን “ጥቁር እንግዳ” ተውኔት ሐሙስ በ12፡00 ሰዓት ለዕይታ ይቀርባል ፡፡
በአብርሃም ገብሬ