AMN – ጥቅምት 27/2017 ዓ.ም
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ከቻይና ባለሥልጣናት ጋር በናይሮቢ ባደረጉት ውይይት ኬንያ ብሪክስን ለመቀላቀል ለምታደርገው ጥረት ቻይና ድጋፍ እንድትሰጥ ጠይቀዋል።
“ከቻይና ጋር ያለን አጋርነት በአፍሪካ ደረጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኬንያ ቁርጠኛ መሆኗን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ” ሲሉ ሩቶ ለቻይና ልዑካን ገልጸዋል።
በተለይም ኬንያ የዓለማችንን 28 በመቶ ኢኮኖሚ የሚሸፍኑ ሀገራት ያሉበትን የብሪክስ ስብስብን ለመቀላቀል የጀመረችውን ጉዞ ቻይና እንድትደግፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ቻይና እና ኬንያ ያላቸውን ስትራቴጂያዊ አጋርነት ተጠቅመው በሀገራቱ የልማት ፐሮጀክቶች እያሳለጡ እንደሚገኙ አፍሪካ ኒውስ ነው የዘገበው።
ብሪክስ በፈረንጆቹ 2006 በብራዚል፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና ቻይና ሀገራት ነው ‘BRIC’ በሚል ስያሜ የተመሠረተው። ደቡብ አፍሪካ ስብስቡን በ2010 ስትቀላቀል ስሙ BRICS’ ሆነ።
ኢትዮጵያ እና ግብጽን ጨምሮ ሌሎች ሀገራት በ2024 የዚሁ ኅብረት አባል መሆናቸው የሚታወስ ነው።
በማሬ ቃጦ