AMN – ጥቅምት 4/2017 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሶማሌ ክልል የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ከወከሉ ተሳታፊዎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ ማካሄድ ጀመረ።
በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ላይ በክልሉ ከ104 ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ ከሶስት ሺህ በላይ የህብረተሰብ ተወካዮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በመክፈቻው ወቅት እንደገለጹት፤ ኮሚሽኑ ባለፉት ጊዜያት በርካታ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
አጅግ መሰረታዊ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ላለመግባባቶች ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን ከምንጫቸው በሀቅና በእውነት በመለየትና አጀንዳ ቀርፆ ምክክር በማድረግ መግባባት ላይ ለመድረስ ታሪክ የምንጽፍበት ሂደት ላይ እንገኛለን ብለዋል።
በተለይም ኮሚሽኑ ከግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮች በተከታታይ እያካሄደ እንደሚገኝም አውስተዋል።
በዚህም በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ፣ በሐረሪ፣ በሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በአፋር ክልሎች የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር መድረኮችን በማሰናዳት ከክልሎቹ ባለድርሻ አካላት የተሰበሰቡትን አጀንዳዎች ተረክቧል።
በአሁኑ ወቅትም በሶማሌ ክልል ከዛሬ ጀምሮ ለቀጣዮቹ ተከታታይ ቀናት የአጀንዳ ማሰባሰብና የምክክር መድረክ በጅግጅጋ፣ ጎዴ እና ዶሎ አዶ ከተሞች የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መርሃ ግብሩ ሀገራዊ መግባባት ሊደረግባቸው ያስፈልጋሉ የሚሏቸውን እጅግ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በህዝባዊ ውይይት አጀንዳ የሚሰበስቡበት ወሳኝ ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
መላው የህብረተሰብ ክፍሎችና የባለድሻ አካላት ተወካዮች በመጪዎቹ ቀናት የሚደረገውን የምክክር እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ፋይዳ በመረዳት በንቃት እንዲሳተፉና ድጋፍ እንዲያደርጉ ኮሚሽኑ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአጀንዳ ማሰባሰቡና የምክክር መድረክ ላይ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ተሳታፊዎችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ልዩ ልዩ ተቋማትና የማህበራት ወኪሎች፣ የመንግስት አስፈፃሚ አካላት፤ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ይገኛሉ ብለዋል።