ወቅቱ ተስፋ የምንቆርጥበት ሳይሆን ተስፋችን እያንሰራራ ያለበት ጊዜ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing ወቅቱ ተስፋ የምንቆርጥበት ሳይሆን ተስፋችን እያንሰራራ ያለበት ጊዜ መሆኑን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN – ግንቦት 18/2017 ዓ.ም

“ትውልድ በመምህራን ይቀረጻል፤ ሀገርም በትምህርት ትበለጽጋለች” በሚል መሪ ሀሳብ በየደረጃው ሲካሄድ የቆየው የመምህራን እና የትምህርት አመራሮች ከተማ አቀፍ ውይይት የማጠቃለያ መድረክ ተካሂዷል፡፡

መምህራንም ከትምህርት ቤት ጀምሮ በየደረጃው ውይይታቸውን ሲያካሂዱ የቆዩ ሲሆን፣ በመዲናዋ የተካሄዱ አጠቃላይ የልማት ስራዎችንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም በአጭር ጊዜ ውስጥ በመዲናዋ የተከናወኑ ሁለንተናዊ የልማት ስራዎች የሚደነቁ እና የመዲናዋን ገጽታ የቀየሩ፣ ብሎም ለኑሮ ምቹ ያደረጉ መሆናቸውን መመልከታቸውን በውይይታቸው ወቅት ገልጸዋል።

በውይይቱ የተሳተፉ የመምህራን ተወካዮች በዋነኛነት የመምህራን እና በትምህርቱ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ አመራሮች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችንም አንስተዋል።

ለአብነትም፡- የመምህራንን የመኖሪያ ቤት ችግር፣ የደሞዝና ጥቅማጥቅም ጉዳይ፣ የደረጃ እድገት እና የትምህርት ደረጃን ማሻሻል፣ የልዩ ድጋፍ እና የአካል ጉዳተኞ መምህራን ግብዓት መሟላት፣ የትምህርት ጥራት መሻሻል እና የመሳሰሉ ጥያቄዎች በመድረኩ ተነስተዋል።

በተለያዩ ወቅቶች መምህራን ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች በከተማ አስተዳደሩ በኩል ፈጣን ምላሾች ሲሰጡ መቆየታቸውን የተናገሩት መምህራኑ፣ የማንም የፖለቲካ ሀይል መጠቀሚያ አንሆንም፤ ጥያቄዎቻችንን በቀጥታ ለአመራሮቻችን በማቅረብ ሞያዊ ግዴታችንን በአግባቡ እየተወጣን የሚሰጠንን ምላሽ በትዕግስት እንጠብቃለን ብለዋል።

የውይይት መድረኩን የመሩት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ አዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ ፕሮጀክቶች ወደ ተጨባጭ ተስፋ የሚያስገቡን ስለመሆናቸው ምልክቶችን እያሳዩን ነው፤ ወቅቱ ተስፋ የምንቆርጥበት ሳይሆን ተስፋችን እያንሰራራ ያለበት ጊዜ ነው ብለዋል።

መምህራን የሚያነሷቸው የኢኮኖሚ እና የማህበራዊ ተጠቃሚነት ጥያቄዎች ትክክል ናቸው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ከተማዋ ካላት አቅም አንጻር በልዩነት ክብርና ትኩረት በመስጠት በፍትሃዊነት የመምህራንን ጥቅማ ጥቅም እያሟላች መሆኗንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ከሚነሱ የመምህራን ጥቅማጥቅም ጥያቄዎች አንጻር በከተማ ደረጃ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገርም የሚታዩ ጉዳዮች ስለሚኖሩ በቀጣይነት ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጋራ እንደሚሰራም ነው ከንቲባ አዳነች የተናገሩት።

በየደረጃው በነበሩ ውይይቶች የተነሱ ጥያቄዎች ተጠንተው እና ታቅደው በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚመለሱት በፍጥነት እንደሚመለሱ፣ በረጅም ጊዜ እና በዘላቂነት የሚመለሱትም ተለይተው በሂደት ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚደረግ ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።

በሰብስቤ ባዩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review