የጠቅላይ ሚኒስትሩን አርአያነት በመከተል ኢትዮጵያውያን የሀገራቸውን ምርት ሊያስተዋውቁ እንደሚገባ ተመላክቷል
ድፕሎማሲ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ግንኙነቶችን በድርድር፣ በንግድ ስምምነቶች እና በባለብዙ ወገን መድረኮች ለመምራት የሚያስችል መሣሪያ ነው። መንግስታት የሀብት አቅርቦትን ለማስጠበቅ፣ ገበያ ለመክፈት እና የውጭ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን እንደሚጠቀሙ አዲሱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ(The New Economic Diplomacy) በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ ህዳር 2 ቀን 2016 ኒኮላስ ቤይን እና እስጢፋኖስ ዎልኮክ ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ ሰፍሯል፡፡
ዲፕሎማሲያቸውን ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ጋር በሰለጠነ መልኩ ያዋህዱ ሀገራት በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው፡፡ ይህም ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ተብሎ ይጠራል፡፡ ዶክተር ፍራንሲስ ቨርጂኒያ አንደርሰን፣ በተባበሩት መንግስታት “INTER GOVERNMENTAL RESEARCH AND POLICY JOURNAL” ላይ እ.ኤ.አ ሚያዚያ 18 ቀን፣ 2025 የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ እና ክልላዊ ውህደት (The Intersection of Economic Diplomacy and Regional Integration) በሚል ርዕስ አንድ ጥናት አሳትመዋል፡፡
በዚህ ጥናት እንደተመላከተው ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት ጉልህ አበርክቶ አለው። ለአብነትም የንግድ ድርድሮችን ቀላል በማድረግ፣ ብዙ የንግድ እንቅስቃሴዎችን በማበረታታት እና በወዳጅ ሀገራት ዘንድ የንግድ ድርጅቶች የሚያስፈልጋቸውን ምርት አሊያም ድጋፍ ግልፅ በማድረግ ትልቅ ሚና ይጫወታል። ኢኮኖሚያዊ ዲፕሎማሲው ደግሞ በሀገራት ታላላቅ መሪዎች የቀጥታ ግንኙነት ሲደረግ ተፈፃሚነቱና ከፍታው በዚያው ልክ ይጨምራል ይላል ጥናቱ፡፡

እንደ መረጃው ከሆነ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ይሄዳሉ፡፡ ይህ ክስተት ባለፉት ጥቂት አሥርት ዓመታት የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲውን ጽንሰ ሐሳብና አሠራር ለውጦታል። በመሆኑም የዲፕሎማሲን እንደ መሰላል በመጠቀም የአንድን ሀገር ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን በውጭ ሀገር ማስቀጠል የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መሰረታዊ ፍቺ ሆኗል፡፡
ሀገራት በዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ፣ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲን እንደ አንድ ወሳኝ መሣሪያ በመጠቀም ውስብስብ የሆነውን የኢኮኖሚ ማነቆዎችን፣ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የንግድ ስምምነቶችን እና ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ አስተዳደርን ለማሳመር ይጠቀሙበታል፡፡
የአፍሪካ ስልጣኔ መግቢያ በር የሆነችው ኢትዮጵያ ደግሞ ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም ከዓለም ሀገራት ጋር ያላት የውጭ ግንኙነት ዘለግ ያለ ዕድሜን አስቆጥሯል።
በተለይ ሀገሪቱ ካለችበት ስትራቴጂካዊ መልክዓ ምድር አቀማመጥ አኳያ፤ ለዲፕሎማሲ ግንኙነት የበለጠ ተመራጭ ሀገር ሆናለች፡፡ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላት ግንኙነትና ተሳትፎም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል ይላሉ ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ መሐመድ በሽር።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ለታ ሴራ( ዶ/ር) በበኩላቸው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ድፕሎማሲ ከፍ እያለ መጥቷል፡፡ ይህንንም እውነት በአራቱ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ግንኙነት መለኪያዎች አብራርተዋል፡፡ የመጀመሪያው መለኪያ የኢንቨስትመንት ፍሰት ነው። በዚህ መለኪያ መሰረትም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በርካታ የውጭ ኢንቨስትሮች ወደ ሀገሪቱ ገብተው እያለሙ ነው። በዚህም ኢኮኖሚውን ከፍ ከማድረግ ባሻገር ለዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ነው።
በግንቦት 4 እና 5 ቀን 2017 ዓ.ም በተካሄደው “2025 የኢንቨስትመንት ፎረም” ላይ የተሳተፉ ከ59 የዓለም ሀገራት የተውጣጡ ባለሀብቶችን ዋቢ አድርጎ የኢትዮጵያ ኢቨስትመንት ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት አዋጭ መዳራሻ ሆናለች፡፡
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባደረጉት ጉብኝትም የኢትዮጵያን ምርቶች ለአብነትም የጫካ ማር፣ ቡና እና መሰል ምርቶችን በጉዟቸው ለሚያገኟቸው ታላላቅ ሰዎች ማስተዋወቃቸው አይዘነጋም፡፡ ይህም የሀገርን ገፅታ ከመገንባት ባሻገር ያሉንን ውድ ሀብቶች ለዓለም የበለጠ የሚያስተዋቅ በመሆኑ በዚያው ልክ የውጭ ኢንቨስትመንትን እንደሚስብም በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ለታ(ዶ/ር)ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መለኪያ ሀገሪቱ ለውጭ ገበያ የምታቀርባቸው ምርቶች ናቸው። ምርቷን በአራቱም የዓለም ማዕዘናት በስፋት ወደ ውጭ እየላከች፤ እየሸጠች ነው። ይህም የሀገሪቱን የውጭ ምንዛሪ አቅም የበለጠ የሚጨምር ነው፡፡
ከኢንዱስትሩ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት እንደ ሀገር ወደ ስራ ከገቡ 104 የውጭ ኢንቨስትመንቶች /ባለሀብቶች መካከል 74 የሚሆኑት በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሰማርተዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ የኢንቨስትመንት ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱን ያሳያል፡፡

ዓመታዊ የዘርፉ ዕድገት በ2014 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 8 በመቶ የነበረው በ2016 በ10 ነጥብ 1 በመቶ አድጓል። በ2017 የበጀት ዓመት በ12 በመቶ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ገቢ ምርት በመተካት በ2014 በጀት ዓመት የነበረው 2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር በ2017 9 ወራት ወደ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር አድጓል፡፡
የፕላን እና ልማት ሚኒስቴር የብሔራዊ አካውንት መረጃ እንደሚያሳየው የማኑፋክቸሪንግ ዕሴት የተጨመረበት ምርት በ2014 በጀት ዓመት ከነበረበት 5 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገደማ፤ በ2016 ወደ 9 ነጥብ 25 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ይህ ከፍተኛ የሆነ ዕሴት ጭማሪ ከላይ የተጠቀሰውን ትክክለኛ የምርት ዕድገት የሚያንፀባርቅ ነው፤ ይላል መረጃው።
ቱሪዝም ደግሞ ሦስተኛው የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መለኪያ ነው። ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ነባሮቹን የበለጠ በማደስና በማስዋብ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችም ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ ለምተዋል፡፡ በዛ ያሉ የውጭ ጎብኚዎች ወደ ሀገሪቱ መጥተው የሀገሪቷን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች እየጎበኙ ነው። እንደ አዲስ አበባ ያሉ ከተሞችም የቱሪስት መሸጋገሪያ መሆናቸው ቀርቶ መዳረሻ ሆነው የበርካቶችን ቀልብ እየገዙና ኢኮኖሚውን ከፍ እያደረጉ እንደሆነም የምጣኔ ሀብት መምህር ለታ ሴራ( ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል፣ ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ባለፉት ዘጠኝ ወራት 84 የሚጠጉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉባዔዎች በአዲስ አበባ ተካሂደዋል፡፡ ለዚህም በከተማዋ የተገነቡ ትላልቅ የስብሰባ ማዕከላት አስተዋጽዖ አበርክተዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 546 ሺ 443 የውጪ ሀገር ቱሪስቶች ከተማዋን መጎብኘታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።
አራተኛው ደግሞ የኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ መለኪያ የልማት ድጋፍ ነው። ኢትዮጵያ በሁሉም ዘርፍ እያሳየች ያለውን ብልፅግና በመመልከትም ዓለም አቀፍ ተቋማት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡ ለአብነትም፡-
የአውሮፓ ኅብረት፣ ዓለም ባንክ፣ አይ ኤም ኤፍ ወዘተ በተመሳሳይ በተለይ ለሰብዓዊ ድጋፍና ለልማት የሚውል በርካታ ድጋፎችን እያደረጉ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ መሐመድ በሽር በበኩላቸው፣ በሀገሪቱ ከመጣው ፖለቲካዊ ለውጥ ጋር ተያይዞ በታሪክ የተሻለ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መፍጠር ተችሏል፡፡ ሌላው ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ትልቅ ተጽዕኖ ያላት ሀገር ናት። ይህም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የበለጠ እየተጠናከረ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሰሞኑ በተለያዩ ሀገራት እያደረጉት ያለው ጉዞና በታላላቅ ሀገራት መሪዎች የተደረገላቸው ሞቅ ያለ አቀባበል ይህንን የሚመሰክር እንደሆነም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መሪዎችም በየዘመናቱ በተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማሲያዊ ጉዞ ማድረጋቸውን ያስታወሱት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልፅግና እያደረጉት ያለው ዓለም አቀፍ ጉዞና ይህንን ተከትሎ በኢንቨስትመንትና መሰል ዘርፎች እንደ ሀገር እየታዩ ያሉ ለውጦች ስኬታማነቱን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል፡፡
እንደ ጃፓን፣ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያን የመሳሰሉ የዓለማችን ታላላቅ ሀገራት በኢኮኖሚ አቅማቸውን ማፈርጠም የቻሉት ዲፕሎማሲያዊ ኢኮኖሚን በመጠቀም ምርታቸውን፣ የተፈጥሮ ፀጋቸውን እና ለኢንቨስትመንት ምቹነታቸውን ለዓለም በማስተዋወቅ ነው፡፡
እንደ ሀገር ከፍ ያለ እና ዘመን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ ቢኖረንም ያለንን ከማስተዋወቅ አንፃር ብዙ አልሰራንም፡፡ ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት፣ መስራት የሚችል ህዝብ እና ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ አሰራር ያላት ሀገር ናት፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች ለማስተዋወቅ እያደረጉት ያለው እንቅስቃሴ የሀገርን ብልፅግና እውን የሚያደርግ ትልቅ እምርታ ነው፡፡ ይህንን አርአያነት በመከተልም በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ሊያስተዋውቁ ይገባል ብለዋል፤ በጅማ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህር ለታ ሴራ(ዶ/ር)፡፡
በመለሰ ተሰጋ