የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት የድጋፍ እና የልማት ማህበር የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሰራዊት ማህበር አባላት በዛሬው ዕለት የመከላከያ ዋና መስሪያ ቤትን ጎብኝተዋል።
ከተሰራው አስገራሚ ኪነ ህንፃ ባሻገር በዙሪያው የሚገኙትን የስራ እንቅስቃሴዎች ተዘዋውረው የተመለከቱት የማህበሩ አባላት በተመለከቱት ተጨባጭ የስራ እንቅስቃሴ እና በተደረገላቸው ገለፃ እጅግ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል።
አካበቢው ውብ ፅዱ እና ማራኪ እንዲሆን ታስቦ ከተከናወኑት ተግባራት ባሻገር ሰራዊቱ በምግብ ራሱን እንዲችል እየተሰሩ ያሉት አሳን ጨምሮ የእንስሳት እርባታ እና በቁጥር በርከታ የሆኑ የአትክልት እና ፍራፍሬ ዝርያዎች በማየታቸው መደሰታቸውን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሀመድን በመወከል መልዕክት ያስተላለፉት የፅህፈት ቤት ሀላፊው ኮሎኔል ግርማ ደምሴ ብሔራዊ የጦር ማህበር አባላት ሀገሪቱ ከውጭም ሆነ ከውስጥ የተቃጣባትን ጥቃት በማምከን የራሳችሁን አሻራ ያሳረፋችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ ኩራት ይገባችኋል ብለዋል።
የማይደበዝዝ ታሪክ ፅፋችሁ ለትውልድ ያስተላለፋችሁ ጀግኖች በመሆናችሁ በማንኛውም ጊዜ ተቋማችን ከጎናችሁ መሆኑን ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ በማለት አጋርነታቸውን አረጋግጠዋል።
የፕሮግራሙ አስተባባሪ የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪ ሌተናል ኮሎኔል ዮሴፍ ለማ እናንተ በአጥንታችሁ እና በደማችሁ ያቆያችኋትን ሀገር የተረከበው መከላከያ ሠራዊት በዘመናዊ ቴክኖሎጅ እና በጠንካራ ስነ ልቦና ሀገሪቱ አሁን በምታዩት ከፍታ ልክ ለማድረሱ መሰረቶቹ እናንተ በመሆናችሁ ክብር ይገባችኋል ብለዋል።
የማህበሩ ፕሬዝዳንት ሀምሳ አለቃ ብርሀኑ አማረ በበኩላቸው ወታደር ለሀገር ክብር ሲል ነፍሱን በፍቃዱ አሳልፎ ለመስጠት የተዘጋጀ ሀይል መሆኑን አንስተው በየዘመናቱ የኢትዮጵያ ወታደር ለእናት ሀገሩ ሉአላዊነት መከበር የራሱን የማይተካ ዋጋ እየከፈለ መምጣቱን መናገራቸዉን ከሃገር መከላከያ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡