
AMN – ጥቅምት 28/2017 ዓ.ም
ወንጀል እና አደገኛ ዕፅ ዝውውርን ለመከላከል ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እና በቅንጅት መሥራት በቀጣናው ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አሺታ ሚታል ገለጹ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አዲስ ከተሾሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅች የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አሺታ ሚታል ጋር ተወያይተዋል።
በውይይታቸው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን የህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣የአደገኛ ዕፅ ዝውውር፣የሀሰተኛ መድኃኒት ዝውውርን፣የህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን፣የኮንትሮባንድ ንግድ እና በሙስና ከአገር የሚሸሽ ገንዘብን በመከላከል ረገድ በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ ከላይ በተገለጹት እና ለቀጣናው ስጋት ደቃኝ ወንጀሎች ዙሪያ ከ.ተ.መ.ድ. የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽ/ቤት ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ዳይሬክተሯ አሺታ ሚታል በበኩላቸው፣ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እና በቅንጅት መሥራት ማለት በቀጣናው ብቻ ሳይሆን እንደ አፍሪካ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ጽ/ቤታቸውም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የየዘርፉ የኢትዮጵያ ተቋማት ጋር በአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ማረጋገጣቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ትክክለኛውን የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዲጂታል ሚዲያ የትስስር አውታሮችን በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑን!