የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የወጣቶች ሚና ለሁለንተናዊ ብልጽግና” በሚል መሪ ሀሳብ በወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአዲስ አበባ ከተማ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከተወጣጡ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል።
በውይይቱም ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ወጣቶች የሀገር ተስፋ፣ አቅም እና ክብር ናቸው ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች ማከናወኑን የገለፁት ከንቲባ አዳነች፣ በዚህም ተጨባጭ ውጤት መገኘቱን ገልፀዋል።
ለአብነት ያክል ወጣቶች በስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በተከናወኑ ስራዎች በ2017 በጀት ዓመት 9 ወራት ብቻ ከሶስት መቶ ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን አፅንዖት ሰጥተዋል።

በተጨማሪም የወጣቶች የስፖርት መዋያ ስፍራዎች እና ሌሎች የወጣቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።
የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
ወጣቶች ለሀገር ሁለንተናዊ ልማት እያበረከቱ የሚገኙትን አስተዋፅዖ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶችም፣ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ስራዎች አስደናቂ እና የወጣቱን ተጠቃሚነት እያረጋገጡ ያሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በዚህም ከልማቱ ጎን በመሆን ሀገራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልፀዋል።
በሀብታሙ ሙለታ