AMN – የካቲት 22/2017 ዓ.ም
ዐድዋ ውስጡንም ውጩንም የቆረጠ ስለት ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚነሲትሩ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ በዐድዋ ዘመቻ ዋዜማ ኢትዮጵያን ከውጭም ከውስጥም ተቀናጅቶ የማዳከም ዘመቻ ነበረ፤ የውጩ የኢትዮጵያን መኖር የማይፈልግ ጠላት ነው፤ የውስጡ ደግሞ ለውጩ ጠላት የሚላላክ ባንዳ ነው፤ የውጩ የኢትዮጵያ ስም የሚለወጥበት አጋጣሚ ዕንቅልፍ የሚነሣው ጠላት ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከነጻነት፣ ከአትንኩኝ ባይነት እና ከጥቁር ሕዝብ ክብር ጋር የተሣሠረ ስም ነው ያሉት አቶ ተመስገን፣ ይሄን ካላጠፋ ዕረፍት የማይገደው፣ ዕንቅልፍ የማይወስደው ጠላት ነው። የውስጡ ሀገር ሲፈርስ ፍርስራሹን በመሸጥ ለመለቃቀም የቋመጠ ተላላኪ እንደሆነም ነው ያመላከቱት፡፡
ዐድዋ ባለ ሁለት ስለት ነው፤ የውጩንም የውስጡ ቆርጧል፤ይህም ኢትዮጵያውያን ሲነሡ የውጭ ባዳ እና የውስጥ ባንዳ እንደማያግዳቸው አሳይቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያዊ የተባለው ኅብረ ብሔራዊ ጦር ከትዕግሥት በኋላ ሲነሣ፤ ከፊቱ የሚቆም እንደሌለ አስመስክሯል ብለዋል።
ዐመል በጉያ ተይዞ ይሟገቱበታል እንጂ ሀገር አያፈርሱበትም፤ ልዩነት ወይ ይከራከሩበታል፣ ወይ ያጌጡበታል እንጂ አይዋጉበትም፣ ይህ ነው የዐድዋ ዘመቻ ልጆች መርሕ።
ከ100ሺ በላይ ሠራዊት፣ ከመላ ሀገሪቱ ተምሞ፤ ሎጀስቲክሱ በሀገር ዐቅም ተደምሮ፤ በቅሎው ተጭኖ፣ ፈረሱ ተገርቶ፣ ስንቁ ተቋጥሮ፣ ያ ሁሉ ቋንቋ በሀገር ፍቅር ተግባብቶ፣ ተአምር ሠርቷል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይሄ ነው በሁለት በኩል የሚቆርጠው ሰይፍ ሲሉም አመላክተዋል።
የዐድዋ ዘመቻ ልጆች ዛሬም አለን፤ እንታገሣለን፤ እንለምናለን፤ ንቀን እናልፋለን፤ በመጨረሻ ግን በሁለት በኩል ለመቁረጥ እንነሣለን ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እንትና ከእንቶኔ ማደማቸው አይገርመንም፤ እኛ የዐድዋ ዘመቻ ልጆች ነን፤ የእቴጌ ጣይቱ ቃል ቃላችን ነው።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “እኔ ሴት ነኝ፤ ጦርነት አልወድም፤ ነገር ግን ሀገሬ እንደዚህ ያለ ክብር የሚነካ ዘለፋ ከምትሸከም ጦርነትን እመርጣለሁ ፤ሂድ መንገዱ ጨርቅ ያድርግልህ፤ እግሩን ለጠጠር ደረቱን ለጦር ሰጥቶ፣ ደሙን ለሀገሩ ፍቅር አፍስሶ፣ እሱ ወድቆ ሀገሩን የማያቆም እዚህ ያለ እንዳይመስልህ ያሉትን የእትጌ ጣይቱ ብጡልን ንግግር በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡
ሂድ የኢትዮጵያን ሰው ባታውቀው ነው፤ ለሀገሩ መሞት ማለት ለሐበሻ ጌጡ ነው፤ ሂድ ባሻህ ጊዜ ተመለስ፤ ተሰናድተን እንጠብቅሃለን፤ ያንተን ወንድነትና የጣይቱን ሴትነትም ያን ጊዜ እናየዋለን፤ ሂድ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፤›› ነበር ያሉት። ይህ ከብዙ ትዕግሥት በኋላ የመጣ ቁጣ መሆኑንም አቶ ተመስገን አመላክተዋል።
ዛሬም ጦርነት አንፈልግም፤ በቂ የጦርነት ታሪክ አለን፤ የሚጎድለን የብልጽግና ታሪክ ነው፣ ስለዚህ ሺ የሰላም መንገዶችን እንሞክራለን፤ እምቢ ከተባልን ግን፣ ምን እናደርጋለን፤ እያዘንንም ቢሆን የእቴጌ ጣይቱን መንገድ እንመርጣለን በማለት እንኳን ለ129ኛው የዓድዋ ድል በዓል በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል።