AMN – የካቲት 29/2017 ዓ.ም
የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ( ማርች 8 ) ታሪካዊ መነሻው የሠራተኞች እንቅስቃሴ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በተመድ ዕውቅና የተሰጠው ዓመታዊ ክብረ በዓል ለመሆን በቅቷል።
የክብረ በዓሉ ጅማሮ በአውሮፓውያኑ 1908 ነበር። በዚህም ወቅት 15 ሺህ የሚሆኑ ሴቶች በኒውዮርክ ከተማ ላይ የሥራ ሰዓት መሻሻል (ማጠር)፣ የተሻለ ክፍያ እና ሴቶች በምርጫ መሳተፍ አለባቸው በሚል የተቃውሞ ሰልፍ በማካሄድ ነበር።
ከአንድ ዓመት በኋላም የአሜሪካ ሶሻሊስት ፓርቲ የመጀመሪያውን ብሔራዊ የሴቶች ቀን (ማርች 8 )ን አወጀ።
ክላራ ዜትኪን የምትባል ግለሰብ ነበረች ቀኑን ዓለም አቀፍ የማድረግ ሃሳብ ያመነጨችው።
ይህ ሀሳብ የተነሳው በዴንማርኳ ኮፐንሃገን በአውሮፓውያኑ 1910 በተካሄደው የሴት ሠራተኞች ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ነበር ።
በዚህ ወቅት ከ17 ሀገራት የተውጣጡ 100 ሴቶች ተሳትፈውበት የነበረ ሲሆን፣ ሁሉም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በሃሳቧ ተስማምተው ነበር።
የሴቶች ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ የተከበረውም በአውሮፓውያኑ 1911 በኦስትሪያ፣ ዴንማርክ፣ ጀርመን እና ስዊዘርላንድ ነበር።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፋዊ ሆኖ መከበር የጀመረው ደግሞ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በዓሉን ማክበር በጀመረበት በአውሮፓውያኑ 1975 ነው።
ለመጀመሪያ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት “የኋላውን ማክበር፤ የወደፊቱን ማቀድ” በሚል መሪ ቃል በ1996 ነበረ በዓለም አቀፍ ደረጃ በደመቀ ሁኔታ የተከበረው።
የሴቶች ቀን ሴቶች በማኅረበሰቡ የደረሰባቸውን ጭቆናን ተቋቁመው በፖለቲካውና በምጣኔ ሀብቱ ያገኙትን ትሩፋት ይዘክራል።
በአሁን ወቅት በዓለም ላይ የሰፈነውን የተዛባ የሥርዓተ-ፆታ ኃይል ሚዛንን ለማስተካከል በተለያዩ ሰልፎችና የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ተከብሮ ይውላል።
በሀገራችን ኢትዮጵያም ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን የተለያዮ ከተሞች በመከበር ላይ ይገኛል።
በወርቅነህ አቢዩ