
AMN ህዳር 20/2017 ዓ.ም
ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በሀዋሳ ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በማስመልከት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሁሪያ አሊ ዛሬ መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በመግለጫቸው ቀኑን በድምቀት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።
ቀኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ የሚከበር ሲሆን ለዚህም አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን አስረድተዋል።
እንደሀገር የአካል ጉዳተኞች መብትን ለማክበርና አካታች በሆነ መልኩ ተጠቃሚነታቸውን ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ እመቤት ኢሳያስ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል።
ቀኑ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እንደሚከበር ጠቁመው፣ ለዚህም ክልሉና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን እንደገለጹ የኢዜአ ዘገባ አመላክቷል።
በዋዜማው አካል ጉዳተኞችና ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎችን ያካተተ የእግር ጉዞ፣ ስፖርታዊ ውድድሮችና የፈጠራ ሥራዎች አውደ ርዕይ እንደሚካሄደም ታውቋል።